Articles – Yetenaweg and Engender Health https://srhr.yetenaweg.com Sexual and Reproductive health and rights (SRHR) in Ethiopia Wed, 06 Mar 2024 14:17:09 +0000 en-US hourly 1 https://wordpress.org/?v=6.6.1 https://srhr.yetenaweg.com/wp-content/uploads/2024/01/yetenawegfinallogo-1-150x150.png Articles – Yetenaweg and Engender Health https://srhr.yetenaweg.com 32 32 የአባላዘር በሽታዎች (SEXUALLY TRANSMITTED INFECTIONS) https://srhr.yetenaweg.com/%e1%8b%a8%e1%8a%a0%e1%89%a3%e1%88%8b%e1%8b%98%e1%88%ad-%e1%89%a0%e1%88%bd%e1%89%b3%e1%8b%8e%e1%89%bd-sexually-transmitted-infections/ Sun, 12 Nov 2023 21:52:30 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3909 በ- ማህሌት አላምነው ሀይሌ (ሚዮንግሳንግ የህክምና ኮሌጅ -1ኛ አመት (PC1)

አርትኦት እና እርማት – በ ዶ/ር ምስክር አንበርብር (Gynecologist/Obstetrician)

 

የአባላዘር በሽታዎች ምንድን ናቸው?

የአባላዘር በሽታ (SEXUALLY TRANSMITTED INFECTIONS) በዋናነት በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች ናቸው። የአባላዘር በሽታ ከሰው ወደ ሰው በደም፣ በግንኙነት ጊዜ በሚፈጠሩ ፈሳሾች፣ እንዲሁም ከእናት ወደ ልጅ በእርግዝና ጊዜ ወይም በውልደት ጊዜም ሊተላለፉ ይችላል።

እንደ አለም ጤና ድርጅት ሪፖርት 30 በላይ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች፣ እና ጥገኛ ተውሳኮች ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች መከሰት ምክንያት ናቸው። የአባላዘር በሽታዎች በአብዛኛው ጊዜ ምልክት አያሳዩም። በዚህም ምክንያት ጤነኛ ተብሎ የሚታሰብ ሰው በቀላሉ በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል።

 

የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ምንድናቸው?

የአባላዘር በሽታዎች በየፊናቸው የተለያዩ ምልክቶች ሊያሳዩም ወይም ላያሳዩም ይችላሉ።

ሊታዩ ከሚችሉ ምልክቶች ወስጥ ከታች የተዘረዘሩት ተጠቃሽ ናቸው፦

  • በብልት እና አካባቢው እብጠት፣ቁስለት እና የህመም ስሜት
  • ሽንት በሚሸናበት ጊዜ ሕመም ወይም የማቃጠል ስሜት
  • ከብልት ያልተለመደ ሽታ እና መልክ ያለው ፈሳሽ ማየት
  • የብልት መድማት
  • በግንኙነት ጊዜ ያልተለመደ የሕመም ስሜት እና
  • ትኩሳት፣ የመሳሰሉት ምልክቶች ተጠቃሽ ናቸው።

የአባላዘር በሽታ ምልክቶች ለበሽታው ከተጋለጡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሊታዩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ለአመታት ከባድ የሚባል ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል።

የተለያዩ አይነት የአባላዘር በሽታዎች አሉ። ከነዚህም መካከል ጥቂቶቹ  የሚከተሉት ናቸው፦

ጨብጥ (GONORRHEA)

በባክቴሪያ የሚመጣ የአባላዘር በሽታ ነው። ጨብጥ የያዘው ግለሰብ በሽንት ጊዜ የማቃጠል ስሜት ሊያሳይ ይችላል። በተጨማሪም ከብልት ውስጥ ነጭ፣ ቢጫ ወይም አረንጓዴ ፈሻሽ ሊወጣ ይችላል። በአብዛኛው ጊዜ ጨብጥ በሴቶች ላይ ምልክት አያሳይም።

 

ቂጥኝ (SYPHILIS)

ቂጥኝ በባክቴሪያ የሚመጣ የአባላዘር በሽታ ነው። በጊዜ ካልታከመ ከባድ የሆነ የጤና ችግሮችን ያስከትላል። ቂጥኝ የሚተላለፈው  በግንኙነት ጊዜ በሚከሰት ንክኪ ነው።

ቂጥኝ የተለያዩ ደረጃዎች አሉት፦

  1. አንደኛ ደረጃ (PRIMARY SYPHILIS) የቂጥኝ የመጀመሪያ ምልክት በብልት አካባቢ ቁስለት ሲሆን ለበሽታው ከተጋለጡ 3 ሣምንት በኋላ ሊታይ ይችላል። ቁስለቱ የህመም ስሜት የለውም እና በሴቶች ላይ የመደበቅ ባህርይ አለው። 3-6 ሳምንት በኋላ ቁስለቱ በራሱ ይድናል።
  2. ሁለተኛ ደረጃ (SECONDARY SYPHILIS) ቁስለቱ ከዳነ ከጥቂት ሳምንት በኋላ በመሉ ሰውነት ላይ የሽፍታ ምልክት ይታያል። በእጅ እና በእግር መዳፍ ላይ ሽፍታ ይስተዋላል።  ሽፍታው የማሳከክ ስሜት የለውም እና በተጨማሪም አንዳንድ ሰዎች የፀጉር መርገፍ፣ የጡንቻ ህመም፣ ትኩሳት እና የጉሮሮ ህመም ያጋጥማቸዋል። እነዚህ ምልክቶች እየመጡና እየጠፉ ለዐመታት ሊቆዩ ይችላሉ።
  3. ሶሰተኛውና ደረጃ (TERITARY SYPHILIS) በጊዜ ህክምና ያላገኙ ታካሚዎች ሌሎች ተጓዳኝ የጤና እክሎች ያጋጥማቸዋል። ከነዚህም መካከል በአንጎል፣ በነርቮች፣ በዓይን፣ በልብ፣ በደም ሥሮች፣ በጉበት፣ በአጥንትና በመገጣጠሚያ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።

 

ክላሚዲያ (CHLAMYDIA)

ክላሚዲያ በባክቴሪያ የሚተላለፍ የአባላዘር በሽታ ሲሆን በቀላሉ የመዳን እድል አለው። እንደ ጨብጥ በሴቶች ላይ ምልክት አያሳይም። የክላሚዲያ ዋነኛ ምልክት በግንኙነት ጊዜ ያልተለመደ የሕመም ስሜት እና ከብልት ያልተለመደ ፈሳሽ ማየት ናቸው።  ክላሚዲያ በጊዜ ካልታከመ በሴቶች እና በወንዶች ላይ መሀንነትን ሊያስከትል ይችላል።

 

የአባላዘር በሽታዎች እና ተያያዥ ጉዳቶች

የአባላዘር በሽዎች ወዲያውኑ ከሚያስከትሉት ጉዳቶች የበለጠ ከባድ ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ለምሳሌ፦

  •   የአባላዘር በሽታ ከእናት ወደ ልጅ ሲተላለፍ የፅንስ መጨንገፍ፣ የተወለዱ ህፃናት የክብደት መቀነስ፣ ወይም የህፃናት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ሊያስከትል ይችላል።
  •   በተጨማሪም የኤችአይቪ ኤድስ ተጋላጭነትንም ይጨምራል

 

የአባላዘር በሽታዎች የመከላከያ መንገዶች

የአባላዘር በሽታዎችን በቀላሉ መከላከል ይቻላል። በተለይም የፆታ ግንኙነት የጀመረ ግለሰብ እራሱን እና አጋሩን እንዴት መጠበቅ እንደሚችል ማወቅ አለበት።

የአባላዘር በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት በቀዳሚነት በፆታዊ ግንኙነት ጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።

  •     በግንኙነት ጊዜ ኮንዶም መጠቀም
  •     የወሲብ አጋር አለማብዛት
  •     መታቀብ
  •     ምርመራዎችን እና ህክምናዎችን ማድረግ
  • በበሽታው የተያዘ ሰው በበሽታው ደግሞ ላለመያዝ እና  የአጋሩን ጤና ለመጠበቅ ለአጋሩ በሽታው እንዳለበት/እንዳለባት  በመግለፅ  አጋሩ ምልክት ባይኖራትም/ባይኖረውም ህክምና አንድታገኝ/እንዲያገኝ ማድረግ ተገቢ ነው።
  • የአባላዘር በሽታዎች ስርጭትን ለመቀነስ በቤት ውሰጥ ወላጆች እና አሳዳጊዎች ከታዳጊ ልጆች ጋር ስለዚህ ጉዳይ በግልፅ ውይይት ማድረግ፣ በትምህርት ቤቶች የስነፆታ ትምህርት ማስፋፋትና ማጠናከር፣ የስነፆታ ጤና መረጃና ትምህርትን በተለይም በአባላዘር በሽታዎች የመተላለፊያ መንገዶች እና የመከላከያ መንገዶችን መረጃ ማቅረብ ይመከራል፡፡

 

የአባላዘር በሽታዎች ምርመራ

የአባላዘር በሽታዎች በአብዛኛው ጊዜ ምልክቶች አያሳዩም። ስለዚህ አብዛኛው በላብራቶሪ ምርመራ ላይ የተመሰረተ ነው። የደም የሽንት እና የፈሳሽ ምርመራ በሽታው መኖሩን እና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ይጠቅማሉ።

ምርመራዎች የበሽታው መኖርና አለመኖሩን ከማረጋገጥ ባለፈም፦

  •   ምልክት የሚያሳዩትን ከማያሳዩት ለመለየት
  •   የፆታዊ ግንኙነት አጋር ተጋላጭነትን ለማረጋገጥ
  •   በእርግዝና ወቅት የፅንሱን ጤንነት ለማረጋገጥ
  •   ከተወለደም በኋላም የህፃኑን ጤንነት ለማረጋገጥ መጠቀም ይቻላል።

 

የአባላዘር በሽታዎች ሕክምና

  • አባላዘር በሽታ ህክምና በሚታዩት ምልክቶች ላይ ይወሰናል። እናም ህክምናውን ለመጀመር አብዛኛውን ጊዜ የላብራቶሪ ምርመራ አያስፈልግም። ሆኖም ግን አንዳንድ ግዜ እነዚህ ምርመራዎች አስፈላጊ ሆነው ከተገኙ በጤና ባለሙያዎች ታዘው ሊሰሩ ይችላሉ።
  • በአሁኑ ጊዜ ለበርካታ የአባላዘር በሽታዎች ዓይነት ውጤታማ የሆነ ሕክምና ማግኘት ይቻላል ክላሚዲያ፣ ቂጥኝ ጨብጥ እና አንድ ጥገኛ ተውሳክ የአባላዘር በሽታ አምጪ (ትሪኮሞኒያሲስ) በነጠላ በሚወስዱ መድሃኒቶች አማካኝነት በአብዛኛው ሊፈወሱ የሚችሉ ናቸው።
  • ለኸርፐስና (HERPES) ለኤች አይ (HIV) በጣም ውጤታማ የሆኑት መድኃኒቶች በሽታውን ሊፈውሱ ባይችሉም የበሽታውን አካሄድ ሊቀንሱ የሚችሉ ፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች አሉ።

በሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፣ የአባላዘር በሽታዎች 9.4% እስከ 21% የሚሆን የስርጭት ስፋት አላቸው። ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብዛኛውን ስፍራ የሚይዙት 15-24 እድሜ ክልል ወስጥ ያሉ ወጣቶች ናቸው በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በወጣቶች ዘንድ የአባላዘር በሽታ  ስርጭት እየጨመረ መጥቷል። በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተካሄደ ጥናት የአባላዘር በሽታ ስርጭት 18.20% መሆኑን አረጋግጧል። ከበርካታ ሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት መፈፀም፣ በጾታ ግንኙነት ወቅት ኮንዶም አመጠቀም፣ እንዲሁም ወጣቶች ስለ አባላዘር በሽታ  ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን ለበሽታዉ መስፋፋት አስተዋፅኦ አድርጓል።

 

SOURCES

  •       World Health Organization. (n.d.). Sexually transmitted infections (stis). World Health Organization. https://www.who.int/health-topics/sexually-transmitted-infections#tab=tab_3
  •       Mayo Foundation for Medical Education and Research. (2023, September 8). Sexually transmitted diseases (stds). Mayo Clinic. https://www.mayoclinic.org/diseases-conditions/sexually-transmitted-diseases-stds/symptoms-causes/syc-20351240
  •       Elizabeth Boskey, P. (n.d.). The most common sexually transmitted infections (stis). Verywell Health. https://www.verywellhealth.com/the-most-common-stds-sexually-transmitted-diseases-3133040
  •       Kassie, B. A., Yenus, H., Berhe, R., & Kassahun, E. A. (2019, November 8). Prevalence of sexually transmitted infections and associated factors among the University of Gondar students, Northwest Ethiopia: A cross-sectional study – reproductive health. BioMed Central. https://reproductive-health-journal.biomedcentral.com/articles/10.1186/s12978-019-0815-5

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

]]>
የወር አበባ ጊዜ ህመም (Dysmenorrhea) https://srhr.yetenaweg.com/%e1%8b%a8%e1%8b%88%e1%88%ad-%e1%8a%a0%e1%89%a0%e1%89%a3-%e1%8c%8a%e1%8b%9c-%e1%88%85%e1%88%98%e1%88%9d-dysmenorrhea/ Sat, 22 Jul 2023 19:36:41 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3751 በረድኤት ወልደሩፋኤል(በቅ/ጳ/ሚ/ሜ/ኮ የ5ኛ አመት ተማሪ)  

By Rediet Wolderufael, C2 (5th year) medical student, SPHMMC

Approved by: Dr. Misikir Anberbir (Gynecologist/Obstetrician) 

 

የወር አበባ ጊዜ ህመም (Dysmenorrhea) ማለት ከየወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ህመም ሲሆን፤ በብዛት የሆድ ቁርጠት እና የወገብ  (የታችኛው ጀርባ) ህመም ስሜት አለው። በአንዳንዶች ላይ የታፋ ህመም ፣ ተቅማጥ፣ የማቅለሽለሽ ስሜት፣ ማስመለስ፣ ራስ ምታት እና ድካም ምልክቶች ሊኖሩት ይችላል።

የወር አበባ ከሚያዩ ሴቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በየወሩ ከ 1 እስከ 2 ቀን ድረስ ሕመም ያጋጥማቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሕመሙ የለዘበ ነው። ይሁን እንጂ ለአንዳንድ ሴቶች ይህ ሕመም በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ በወር ውስጥ ለበርካታ ቀናት የተለመደውን እንቅስቃሴያቸውን እንዳያከናውኑ ይከለክላቸዋል።

ሁለት አይነት የወር አበባ ጊዜ ህመም አሉ። እነዚህም፦

  • ከበሽታ ጋር ያልተያያዘ የወር አበባ ጊዜ ህመም (Primary Dysmenorrhea) እና
  • ከበሽታ ጋር የተያያዘ የወር አበባ ጊዜ ህመም (Secondary Dysmenorrhea)

ከበሽታ ጋር ያልተያያዘ (Primary Dysmenorrhea) የሚከሰተው ፕሮስታግላንዲን በተባሉ ከማህፀን ግድግዳ ላይ ባሉ ተፈጥሯዊ ኬሚካሎች ምክንያት ነው። እነዚህ ኬሚካሎች (ፕሮስታግላንዲኖች) የማህፀን ጡንቻዎችና የደም ሥሮች እንዲኮማተሩ ያደርጋሉ። ‍ይህ መኮማተር ለህመሙ መንስኤ ይሆናል። የነዚህ ፕሮስታግላንዲኖች (ኬሚካሎች) መጠን የወር አበባ የመጀመሪያ ቀናት ላይ ከፍተኛ ስለሆነ ሕመሙም ከፍተኛ ነው። የደም መፍሰስ እየቀጠለና የወር አበባ እየፈሰሰ ሲሄድ የፕሮስታግላንዲኖች መጠን ይቀንሳል። ሕመምም ከመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በኋላ የሚቀንሰው ለዚህ ነው። ይህ የወር አበባ ጊዜ ህመም የሚጀምረው አንዲት ልጅ የወር አበባ ማየት ከጀመረች ብዙም ሳይቆይ ነው። ብዙ ሴቶች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የወር አበባ ጊዜ ህመም እየቀነሰ ይመጣል። ይህ ዓይነቱ ሕመም ከወሊድ በኋላም ሊሻሻል ይችላል።

ከበሽታ ጋር የተያያዘ (Secondary Dysmenorrhea) የሚከሰተው በመራቢያ አካላት ላይ በሚከሰት የጤና እክል ምክንያት ነው። ሕመሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ከተለመደው የወር አበባ ቁርጠት የበለጠ ጊዜ ይቆያል። በተጨማሪም ሕመሙ የሚጀምረው የወር አበባ ከመጀመሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ሊሆን ይችላል። ሕመሙ እየተባባሰ ሊሄድና የወር አበባ መፍሰስ ካቆመ በኋላ ላይጠፋ ይችላል።

 

የወር አበባ ጊዜ ህመም እንዴት ማከም እንችላለን?

የወር አበባ ጊዜ ህመምን በርካታ የቤት ውስጥ ዘዴዎች ፣ የሕመም ማስታገሻ እና የሆርሞን ህክምና(hormonal therapy) በመጠቀም ማከም ይቻላል።

 

የቤት ውስጥ ዘዴዎች

  1. ሙቀት-በታችኛው ሆድ ላይ ማሞቂያ ፓድ ወይም ሙቅ ውሃ የያዘ ጠርሙስ በመጠቀም ማሞቅ ህመምን በእጅጉ ሊቀንስ ይችላል። የሕመም መቀነስ አቅሙም ከማስታገሻ መድሃኒት ጋር ተወዳዳሪ ሲሆን የማስታገሻ መድሃኒት እና ሙቀትን በጋራ መጠቀም የበለጠ ህመም የማጥፋት አቅም አለው። በጣም ሞቃት በሆነ የማሞቂያ ፓድ ወይም ትኩስ የውሃ ጠርሙስ ቆዳን ከማቃጠል መቆጠብ አስፈላጊ ነው፤ በግምት 40ºC (ለሰስ ያለ) ሙቀትን መጠቀም ይመከራል። ሙቀቱ አስፈላጊ ሆኖ በሚታሰብበት ጊዜ ሁሉ ልንጠቀመው እንችላለን።
  2. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ- በሳምንቱ ውስጥ አብዛኛውን ቀን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ከማረግ ባለፈ ሕመምን የሚያግዱ ኬሚካሎችን ለማምረት ይረዳል። ለዚህም እንደ መራመድ፣ የሶምሶማ ሩጫ ፣ ሳይክል መንዳት ወይም መዋኘት የመሳሰሉት የኤሮቢክ እንቅስቃሴዎች ይመከራሉ።
  3. እንቅልፍ- ከወር አበባ በፊትና ወቅት በቂ እንቅልፍ መተኛት አስፈላጊ ነው። ጥሩ እረፍት ማግኘት የወር አበባ ጊዜ የሚያጋጥምን ህመም ለመቋቋም ሊረዳ ይችላል።

 

የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች

የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች (NSAIDs)-ህመምን እና ትኩሳትን የሚቀንሱ መድሃኒቶች ሲሆኑ፤ ከየወር አበባ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሕመምን በመቀነስ ረገድ በጣም ውጤታማ የሆኑ መድኃኒቶች ናቸው። አንዳንድ የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች (NSAIDs) ያለ ሐኪም ማዘዣ መገኘት ይችላሉ፤ ከነዚህም አይቡፕሮፌን(Ibuprofen) በዋናነት ይጠቀሳል። እነዚህ መዳኒቶች (NSAIDs) የደም መፍሰስ ወይም ሌሎች የወር አበባ ምልክቶች እንደጀመሩ ወይም ከጀመሩ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት ባለ ጊዜ በቋሚ ፕሮግራም ከተወሰዱ በጣም ውጤታማ ናቸው ። የደም መፍሰስ ችግር፣ አስም፣ አስፕሪን አለርጂ፣ የጉበት ጉዳት፣ የኩላሊት ጉዳት፣ የአንጀት ቁስል፣ የጨጓራ ቁስል እና የመሳስሉት ተያያዥ በሽታ ያለባቸው ሰዎች እነዚህን የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች (NSAIDsን) መውሰድ የለባቸውም። በተጨማሪም ስለ የወር አበባ ጊዜ ህመምን ማስታገሻ ጉዳይ ሃኪም ማማከር ይኖርባችዋል።

 

የሆርሞን ህክምና (hormonal therapy)  

  • የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች (ኪኒኖች) እና ሌሎች የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች (ለምሳሌ፡ መርፌ፣ ሉፕ (IUD) እና የቆዳ ስር የሚቀመጠው የወሊድ መከላከያ (ኢምፕላንት) የወር አበባ ጊዜ ህመም ላላቸው ሴቶች ውጤታማ ህክምናዎች ናቸው። እነዚህ መድሀኒቶች ፕሮስታግላንዲንን (ማህፀን እንዲኮማተር የሚያደርገው ኬሚካል) የሚያመርተው የማህፀን ግድግዳ በመቀነስ ሕመም፣ ቁርጠትና የወር አበባ መፍሰስ እንዲቀነስ ያደርጋሉ። ይህ ዘዴ በተለይ እርግዝናን መከላከል ለሚፈልጉ ሴቶች በጣም ጠቃሚ ነው ። ነገር ግን የወሲብ ግንኙነት የማያረጉ ሴቶችም ሊጠቀሙበት ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ህክምናን ከሁለት እስከ ሶስት ወር ከተጠቀሙ በኋላ ከፍተኛ ለውጥ ይኖራቸዋል።
  • ሉፕ (IUD)- ሌቭኖርገስትሬል (ሚሬና) የተባለውን ሆርሞን የያዘው ሉፕ (IUD) ከላይ እንደተጠቀሱት የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች እና ሌሎች የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች የወር አበባ ጊዜ ህመምን 50 በመቶ ሊቀንስ ይችላል።

በተጠቀሱት ዘዴዎች ሕመሙ በበቂ ሁኔታ ካላስታገሰ ምን ማድረግ እንችላለን?

  1. ለየወር አበባ ጊዜ ህመም በጣም ውጤታማ የሆኑ ህክምናዎች የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች(NSAIDs) ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ ኪኒኖች እና ሌሎች የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ናቸው። ከእነዚህ የሕክምና ዓይነቶች አንዱ በሁለት ወይም በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕመሙን በበቂ ሁኔታ ካላስታገሰው ሌላ ሕክምና ሊሰጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ሴት የሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች (NSAIDs) ሞክራ የወር አበባ ጊዜ ህመም ካልታገሰ፣ በሕመም ማስታገሻ መድሀኒቶች ምትክ ወይም በተጨማሪ የሆርሞን የወሊድ መቆጣጠሪያ ልትወስድ ትችላለች።
  2. ከላይ የተጠቀሱት መንገዶች ሕመምን በሚገባ ካላሻሻሉ ቀጣዩ እርምጃ ከበሽታ ጋር የተያያዘ (Secondary Dysmenorrhea) ሊሆን ስለሚችል የወር አበባ ጊዜ ህመም መንስኤዎችን መመርመር እና ማከም ነው። ለዚህም ህክምና ቦታ በመሄድ ተገቢውን ምርመራ እና ህክምና ማግኘት ተገቢ ነው።

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

]]>
ማረጥ (Menopause) https://srhr.yetenaweg.com/%e1%88%9b%e1%88%a8%e1%8c%a5-menopause-%e1%88%9d%e1%8a%95%e1%8b%b5%e1%8a%95-%e1%8a%90%e1%8b%8d/ Sat, 22 Jul 2023 18:55:32 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3738 በዶክተር ቤተልሄም ተስፋስላሴ(ጠቅላላ ሀኪም)

By Dr.Bethlehem Tesfaselassie General Practitioner

Reviewed and Approved by Dr.Misikr Anberbir (Gynecologist/Obstetrician)

 

ማረጥ (Menopause) ምንድን ነው?

  • ማረጥ ከእድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣ ተፈጥሯዊ ሂደት ሲሆን ፤ ሴቶች የወር አበባ ማየት የሚያቆሙበት ጊዜ ነው።
  • አንዲት ሴት አረጠች የሚባለው ለ 12 ወራት ወይም ለአንድ አመት እና ከዚያ በላይ የወር አበባ ሳታይ ስትቆይ ነው። ይህም የመውለጃ ግዜ ማብቃቱን ያመላክታል።
  • አብዛኛዎቹ ሴቶች ከ 45 እስከ 55 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ማረጥ ያጋጥማቸዋል። ሆኖም ግን በአንዳንድ ሴቶች ላይ ማረጥ ከ40 አመት በፊት ሊከሰት ይችላል። ለዚህም የተለያዩ የጤና እክሎች መንስኤ ይሆናሉ።
  • ማረጥ የሚከሰተው ኦቫሪ የሚባለው እንቁላል አምራች አካል ኢስትሮጅን (Estrogen )ማምረት ሲያቆም ነው። ኢስትሮጅን የወር አበባ ዑደትን ለመቆጣጠር የሚረዳ ሆርሞን (ንጥረነገር) ሲሆን ፤ የዚህ ንጥረ ነገር ማነስ በዚህ ወቅት ለሚታዩ የሰውነት ላይ ለውጦች መከሰት ዋነኛ ምክንያት ነው።
  • የማረጥ ሽግግር ቀስ በቀስ ሆኖ አመታት ሊወስድ ይችላል። ይህ ሽግግር ብዙውን ጊዜ በወር አበባ ላይ ለውጦችን በማየት ይጀምራል። ለምሳሌ፦ የወር አበባ ከተለመደው በተለየ መልኩ ቶሎ ቶሎ መምጣት ወይም መዘግየት፣ በመጠን መብዛት ወይም ማነስ። ምንም እንኳን እነዚህ ምልክቶች ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ሊሆኑ ቢችሉም፤ የተለያዩ አሳሳቢ የጤና ችግሮች ተመሳሳይ ምልክት አላቸው። ስለዚህ አንዲት ሴት እነዚህን ምልክቶች ካየች ችላ ሳትል የጤና ባለሙያ ማማከር አለባት!

 

የወር አበባ ዑደት ከመቀየያር በተጨማሪ የማረጥ ሌሎች ምልክቶች ምንድን ናቸው?

  • በፊት እና ላይኛው የሰውነት አካል ላይ የሚሰማ ድንገተኛ የሙቀት ስሜት እና ላብ ፦ይህ ስሜት ከጥቂት ሴኮንዶች እስከ ብዙ ደቂቃዎች ወይም ከዚያ በላይ ሊቆይ ይችላል። አንዳንድ ሴቶች በወር ውስጥ ጥቂት ጊዜ ሲያጋጥማቸው ሌሎች ደግሞ በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ።
  • የእንቅልፍ ችግሮች፦ እንቅልፍ ማጣት (መተኛት መቸገግር) ወይም ከተለመደው ጊዜዎ በፊት መንቃት። የሌሊት ላብ እንቅልፍንም ሊረብሽ ይችላል።
  • የብልት መድረቅ ፣ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢንፌክሽኖች መጋለጥ እና በወሲብ ወቅት ህመም መሰማት
  • የሽንት ቱቦ መቆጣት ፣ ቶሎ ቶሎ ሽንት መምጣት፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መጋለጥ
  • የአጥንት መሳሳት (ኦስቲዮፖሮሲስ)፦ከ 35 አመት በኋላ ትንሽ መጠን ያለው አጥንት መሳሳት በወንዶችም በሴቶችም ላይ የተለመደ ነው። ነገር ግን ከማረጥ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 4-8 ዓመታት ውስጥ በሴቶች ላይ የአጥንት መሳሳት ፍጥነት ይጨምራል። ይህ የሚከሰተው የኢስትሮጅን መጠን በመቀነሱ ሲሆን ለአጥንት ስብራት ያጋልጣል። አብዛኛውን ጊዜ የጭን ፣ የእጅ አንጓ እና የአከርካሪ አጥንቶች ይጎዳሉ።
  • የመንፈስ ጭንቀት፣ ድባቴ መሰማት
  • ኤስትሮጅን የልብ በሽታ (heart attack) እና በአንጎል ውሰጥ የደም መፍሰስን (stroke) ይከላከላል። ከማረጥ በኋላ የዚህ ንጥረነገር ማነስ የእነዚህ በሽታዎች ተጋላጭነትን ይጨምራል። ከዚህ ምክንያት በተጨማሪ ይህ የእድሜ ክልል ሌሎች ለልብ በሽታ የሚያጋልጡ ምክንያቶች (እንደ የአካል ብቃት መቀነስ ፣ ስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን እና የደም ግፊት) የበዙበት ጊዜ ነው። እነዚህ ሁሉ ተጣምረው በማረጥ ላይ ባሉ ሴቶች ላይ የልብ በሽታ (heart attack) እና በአንጎል ውሰጥ ደም መፍሰስ (stroke) መከሰት እድልን ይጨምራሉ።

 

በማረጥ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች የወር አበባ ማየት ከመቆም ውጭ ምንም ምልክት አይታይባቸውም ወይም ጥቂት ቀላል ምልክቶች ብቻ ይኖራቸዋል። ሌሎች ደግሞ ከባድ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ምልክቶች አሏቸው። እነዚህ ምልክቶች ከሚፈጥሩት አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ተፅእኖ የተነሳ ህክምና ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

ማረጥ ተፈጥሯዊ ሂደት ስለሆነ ምንም ዓይነት ሕክምና አይጠይቅም ። ከዚህ ይልቅ ሕክምናዎች የሚያተኩሩት ምልክቶችን በማስታገስ እንዲሁም ከእድሜ መጨመር ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ ሥር የሰደዱ ሁኔታዎችን በመከላከል ወይም በማከም ላይ ነው።

 

የማረጥ ምልክቶችን እንዴት በራሳችን መቆጣጠር እንችላለን?

  • በፊት እና ላይኛው የሰውነት አካል የሰውነት ላይ ድንገተኛ የሙቀት ስሜት ሲሰማ ቀዝቃዛ ውኃ መጠጣት ወይም ወደ ቀዝቃዛ ቦታ መሄድ እና ይህን ስሜት የሚቀሰቅሰው ምን እንደሆነ ለማወቅ መሞክር ያስፈልጋል። ለብዙ ሴቶች ትኩስ መጠጦች፣ ቡና (ካፌይን)፣ ቅመም ያላቸው ምግቦች፣ የአልኮል መጠጥ፣ ውጥረት(stress)፣ ሞቃታማ የአየር ጠባይ እና ሞቅ ያለ ክፍል ምልክቶቹን ያባብሳሉ።
  • በቂ እንቅልፍ መተኛት ፣ ቡና ከመውሰድ መቆጠብ( እንቅልፍን ስለሚያደናቅፍ)
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፦ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የልብ ሕመምን፣ የስኳር በሽታን፣ የአጥንት መሳሳት እና እድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል ያስችላል።
  • የተመጣጠነ ምግብን መመገብ፦ እነዚህም የተለያዩ ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችንና ጥራጥሬዎች፣ የእንሰሳት ተዋፅኦዎች (ወተት እና የ መሳሰሉት) ያካትታል። ቅባት፣ ዘይትና ስኳር ገደብ ማበጀት። ጠንካራ አጥንትን ለመጠበቅ የሚረዳ በቂ ካልሲየም እና ቫይታሚን ዲ በአመጋገብ ውስጥ ማካተት።ካልሲየም ወይም ቫይታሚን ዲ የሚያስፈልግ ከሆነ መውሰድ።
  • አለማጨስ፦ ማጨስ በልብ በሽታ፣ በአንጎል ውስጥ ደም በመፍሰስ፣ የአጥንት መሳሳት፣ በካንሰርና በሌሎችም የተለያዩ የጤና ችግሮች የመያዝ አጋጣሚያን ከፍ ያደርጋል።
  • አልኮል መጠጥን መቀነስ

ከላይ ያየናቸውን ዘዴዎች ምልክቶቹን ካላስታገሱና የማረጥ ምልክቶች በአንዲት ሴት ላይ ተፅእኖ ካሳደሩ የሆርሞን ቴራፒ (ህክምና) ይደረጋል።

 

የሆርሞን ህክምና (Hormonal therapy) ምንድን ነው?

  • ሆርሞን ህክምና ማለት ኤስትሮጅን የተባለውን ንጥረነገር በመድሀኒት መልክ ለብቻው ወይም ከሌላ ሆርሞን (ኘሮጀስትሮን) ጋር አጣምሮ የሚሰጥ ህክምና ነው።
  • የሆርሞን ቴራፒ ማረጥ ምልክቶችን ለማስታገስ ይረዳል።
  • ኤስትሮጅን በተለያዩ መልክ ሊሰጥ ይችላል። (እንክብሎችን፣ የቆዳ ላይ በሚለጠፉ ንጣፎችን ወዘተ)
  • የብልት መድረቅ ብቻ ያጋጠማቸው ሴቶች ይህ መድሀኒት እዛው አካባቢ ላይ እንዲቀቡ ተደርጎ በክሬም መልክ ሊታዘዝ ይችላል።

 

የሆርሞን ህክምና ጥቅሞች ምንድ ናቸው?

  • ድንገተኛ የሙቀት ስሜትን ለማስታገስ
  • የብልትን መድረቅ እና በወሲብ ወቅት ህመም መሰማትን ለማስወገድ
  • የአጥንት መሳሳት ለመከላከላል
  • የተቀናጀ ኤስትሮጅንና ፕሮጄስቲን ሕክምና የአንጀት ካንሰርን አደጋ ሊቀንስ ይችላል። ሆኖም ግን የሆርሞን ቴራፒ የተወሰኑ የካንሰር ዓይነቶችን እና ሌሎች ሁኔታዎችን አደጋ ይጨምራል።

ከላይ ካየናቸው ህክምናዎች በተጨማሪ በአእምሮ ጤንነት ላይ ስለሚታዩ ለውጦች ከሐኪም ጋር መወያየት ተገቢ ነው። የቤተሰብ አካላዊ እና ሰነ-ልቦናዊ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም መዘንጋት አይገባም።

በመጨረሻም በዚህ የእድሜ ክልል ውሰጥ ያለች ሴት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የተለያዩ የጤና ምርመራዎች እንድታደርግ ይመከራል። አነዚህም የደም ግፊት ፣ የስኳር መጠን መለካት፣ የተለያዩ የካንሰር ቅድመ ምርመራዎች ማድረግ (የጡት፣ የአንጀት፣ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር…ወዘተ) ናቸው።

 

ምንጮች፦

The Menopause Years | ACOG

Menopause (who.int)

Menopause – Diagnosis and treatment – Mayo Clinic

 

የጤና ወግ

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

]]>
የጡት ማጥባት ጥቅሞች | Breast Feeding https://srhr.yetenaweg.com/%e1%8b%a8%e1%8c%a1%e1%89%b5-%e1%88%9b%e1%8c%a5%e1%89%a3%e1%89%b5-%e1%8c%a5%e1%89%85%e1%88%9d-breast-feeding/ Thu, 09 Feb 2023 03:11:45 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3358 Written by በእምነት የሻው ሳልህ (በቅ/ጳ/ሚ/ሜ/ኮ የ5ኛ አመት ተማሪ)

Bemnet Yeshaw Saleh, 5th year medical student at St Paul hospital millennium medical college.
Reviewed by Dr. Wuhib Zenebe

 

የመጀመሪያ ሳምንት ላይ…

እንኳን ደስ አለሽ! አሁን ልጅሽን ፈጣሪ ረድቶሽ በሰላም ተገላግለሻል፡፡ ከዚህ በኋላ ለሚኖረው የጡት ማጥባት ቆይታሽም እጅግ ጠቃሚዎቹ ጊዜያት እነዚህ የመጀመሪያ ቀናቶች ናቸው፡፡ በጥሩ ሁኔታ ማጥባት ከጀመርሽ በጥሩ ሁኔታ የመቀጠል እድልሽ ሰፊ ይሆናልና፤ እንዲሁም መጀመሪያ በደንብ ካጠባሽ ወደፊት ጡትሽ በቂ ወተት ይኖረዋል የሚል ተፈጥሯዊ ሕግ ስላለ ምንም እንኳን እነዚህ ቀናት በሕይወትሽ ትልቅ ለውጥ የምታስተናግጂባቸው እና ከባድ ቢሆኑም ልጅሽን በማጥባት የሚቀጥሉትን ጊዜያቶች የተስተካከሉ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ይህንን የመጽሐፉን ክፍል ስታነቢ ልጅሽ ከሁለት ሳምንት አልፏት ቢሆን እንኳን ይህ ክፍል አይመለከተኝም ብለሽ እንዳትዘዪው፤ ምናልባት አስተያየትሽን ሰፋ ሊያደርግልሽ ስለሚችል ማለት ነው፡፡

በመጀመሪያዎቹ ቀናት ጤነኛ የአመጋገብ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ልክ ሕጻኗ ልጅሽ እንደተወለደች ካንቺ ጋር ለተወሰነ ጊዜ በመነካካት መቆየት ስላለባት ሆድሽ ላይ እንድትተኛ ይደረጋል፡፡ ከተወለደች በኋላ ባለው የአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥም ጡት ማጥባት አስጀምሪያት፡፡ ልጅሽ በዚህ ጊዜ እንገር ታገኛለች። ይህ የመጀመሪያው ከጡትሽ የሚወጣው ቢጫ ቀለም ያለው ወፈር ያለ ወተት ነው ፤ ሕጻኗ ልጅሽን ከተለያዩ በሽታዎች ይጠብቃታል፡፡

በመጀመያው ሳምንት የሚኖረው የማጥባት ሁኔታ በሁለተኛው ሳምንት እና ከዚያ በኋላ ከሚኖረው ጋር ሰፋ ያለ ልዩነት ሊኖረው ይችላል፡፡ እስካሁን የሰማሽውና ያነበብሽው ነገር አብዛኛው ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ ያለውን የሚመለከት ነው፡፡ 

ገና የተወለደችው ጨቅላ ሕጻን ልጅሽ  ከወሊድ በፊት ተርባ አታውቅም ነበር፤ የምግብ(ንጥረነገር) ፍላጎቷ በቋሚነት በእትብት በኩል ይሟላላት ነበር፡፡ ከወሊድ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ረሃብ ምን ማለት እንደሆነ ታያለች፡፡ የሥርዓተ ልመትን (digestive system) መጠቀም እና በጊዜ የተገደበ መብልም ለሷ አዲስ ነው፡፡ 

ታዲያ ልጅሽ የምታሰተናግደውን ተፈጥሯዊ ለውጥ ቀለል ለማድረግ ቀስ በቀስ፣ በትንሽ በትንሹ ማጥባት ትጀምሪያለሽ፤ የልጅሽ ጨጓራ በእያንዳንዱ የመጥቢያ ጊዜ ከ5 እስከ 10 ሚሊ ሊትር ብቻ ነው መያዝ የሚችለው፣ የሚደንቀው ነገር በዚህ ጊዜ በጡትሽ ውስጥ ተዘጋጅቶ ያለው እንገርም መጠኑ ይህን ያህል ነው፡፡ ከሚበቃት በላይ ወተት ብታጠጫት፣ ጨጓራዋ የመለጠጥ አቅምም ስለሌለው መልሶ ወደ ውጪ መውጣቱ ነው፡፡

መች መች ላጥባት?

ገና የተወለደችው ልጅሽ በጣም እንቅልፋም በመሆኗ መመገብ በሚያስፈልጋት ጊዜ ሁሉ የመፈለግ ምልክቶችን ላታሳይሽ ትችላለች፡፡ ስለዚህ ፍላጎት ባሳየች ጊዜ ሁሉ አጥቢያት፤ ነገርግን በ24 ሰዓት ውስጥ ቢያንስ 8 ጊዜ ትጥባ፡፡ በተደጋጋሚ ማጥባት ጡትሽንም የበለጠ ወተት እንዲያመርት እንደሚያደርገው አትርሺ፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው ልጅሽ ሲርባት/ ምግብ ስትፈልግ ምልክቶችን ታሳይሻለች (ምንም እንኳን በመጀመሪያው ሳምንት በተገቢው ጊዜ ሁሉ ባታሳይም)፡፡ ሕጻናት እንደራባቸው ለማወቅ የግድ እስከሚያለቅሱ መጠበቅ የለበትም፡፡ ማልቀስ የልጅሽን ረሃብ የሚያመለክት ዘግይቶ የሚመጣ ምልክት ስለሆነ ሕጻኗ እዚህ ደረጃ ሳትደርስ እንድትመግቢያት ይመከራል፡፡ ታዲያ ከማልቀስ ቀደም ብለው የሚመጡ ምልክቶች፡

  • አፏን በደንብ በመክፈት ራሷን ከአንድ ጎን ወደ ሌላ ማመላለስ (ጡት እየፈለገች መሆኑ ነው)
  • እጇን ወደ አፏ መክተት
  • መንጠራራት እና እንቅስቃሴ ማብዛት
  • የመጨናነቅ/ የመረበሽ ስሜት ማሳየት ናቸው፡፡

ሕጻናት ገና እንደተወለዱ አካባቢ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሊጠቡ ይችላሉ፡፡ ለአንድ ወይም ሁለት ቀን በጣም በተደጋጋሚ ሊጠቡ፣ በሌሎች ቀናት ደግሞ በቀን ትንሽ ጊዜ ብቻ ሊጠቡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ አንድ ሕጻን ከሌላ ሕጻን ቢለያይም አብዛኞቹ ግን ከአንድ እና ከሁለት ሳምንት በኋላ ቋሚ የመጥቢያ ሰዓቶችን / ድግግሞሽን እየያዙ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ አካባቢ በ24 ሰዓት የምትመገብበትን ድግግሞሽ መቁጠርና መቆጣጠርሽ እንደተጠበቀ ሆኖ በመጥቢያ ሰዓቷ መካከል የሚኖረውን ክፍተት ግን ብዙ አትጨነቂበት፡፡ ሕጻኗ ትንሽ አደግ እስከምትል ቋሚ የመመገቢያ ጊዜ እንዲኖራት አትጠብቂ፡፡ (ልጅሽ በየግማሽ ሰዓቷም የምትጠባበት ጊዜ ይኖር ይሆናል!!)

የሽንት ጨርቅ

የሽንት ጨርቅን በተመለከተ በደንብ እየጠባች ያለች ሕጻን በቀን ቢያንስ 6 ዳይፐሮችን/ የሽንት ጨርቆችን እያራሰች ታስቀይርሻለች፡፡ ይህ ግን ከትንሽ ጊዜ በኋላ ነው እውነት የሚሆነው፤ ለጊዜው ግን ትንሽ ለየት ያለ ነገር ይኖራል። በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሕጻኗ የምትወስደው ወተት ትንሽ በመሆኑ፣ የምታስቀይርሽ ዳይፐርም እንዲሁ አነስ ያለ ይሆናል፡፡ ይህ እስከ 3ኛ እና 4ኛ ቀን ድረስ ይቀጥላል፡፡ በአንደኛው ሳምንት መጨረሻ ላይ ልጅሽ የምትጸዳዳበት መጠን ስትወለድ ከነበራት በዐሥር እጥፍ ሊጨምር ይችላል፡፡ 

 

ከልጄ ጋር በአንድ አልጋ እንተኛ?

ከጤነኛ ወሊድ በኋላ እናትና ልጅ ተለያይተው እንዲተኙ ባለሙያዎች አይመክሩም፡፡ ባስፈለገ ጊዜ ሁሉ ልጅሽን ለመመገብ፣ እቅፍ ለማድረግ እና ለማጽዳት ከልጅሽ ጋር በአንድ አልጋ፣ ካልሆነም በአንድ ክፍል መተኛት ይኖርብሻል፡፡ ስለዚህ ልጅሽን ካንቺ ጋር በአንድ አልጋ አስተኚያት፣ አሊያም ደግሞ በሕጻን አልጋ አድርገሽ ካንቺ አጠገብ አስተኚያት፡፡

በተለይ በሀገራችን አብዛኞቹ ጡት የሚያጠቡ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር እጅግ የተቆራኘ የዕለት ዕለት ኑሮ ስላላቸው ይህንን ጉዳይ ማንሳት ምናልባት ለቀባሪ እንደ ማርዳት ሊሆንብን ይችላል፡፡ ለአንድ ሕጻን ከእናቱ ጋር በአንድ አልጋ መተኛት ለደኅንነቱ አስጊ እንደሆነ የሚነገርበትም ጊዜ አለ፡፡ በእርግጥም ይህንን የሚጠቁሙ አንዳንድ ጥናቶችም አሉ፤ ሌሎች በቅርብ ጊዜ የወጡ ጥናቶች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው በአንድ አልጋ መተኛት ችግር እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ምንም እንኳን በባለሙያዎቹ ዘንድ አወዛጋቢ ቢሆንም ግን እጅግ ለረዥም ጊዜ በእናቶች ሲተገበር የነበረ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ከሕጻኗ ልጅሽ ጋር በአንድ አልጋ የምትተኚ ከሆነ ግን የሚከተሉትን ነገሮች ተጠንቀቂ፡

  • መጠጥ ጠጥተሽ ከሆነ ከልጅሽ ጋር አብረሽ እንዳትተኚ
  • ሲጋራ የምታጨሺ ከሆነ አቁሚ
  • አልጋ ላይ እንጂ ሶፋ ላይ ልጅሽን ይዘሽ እንዳትተኚ

 

የጡት ማጥባት ጥቅም ምንድነው?

አንድ የማይቀለበስ እውነት የጡት ወተት ለጨቅላ ሕጻንሽ እጅግ ተመራጭ የሆነው ምግቧ መሆኑ ነው፡፡ የጡት ወተት ለልጅሽ እድገት እጅግ የተስማማ ነው፡፡አንቺ በተገቢው መንገድ የምትመገቢ ከሆነ፣ የጡትሽ ወተት በኃይል ሰጪ ካሎሪዎች እና በሌሎች የተመጣጠኑ ንጥረነገሮች የተዋቀረ ይሆናልና እስከ ስድስት ወር የሚያስፈልጋትን ነገር ሁሉ ያሟላላታል፡፡

የጡት ወተት በውስጡ የእናቲቱን የዓመታት ትዝታ እና እውቀትን ይይዛል! ይህም ማለት አንቺ በሽታን የተዋጋሽባቸውን ጥበቦች የያዙት ወታደሮች በጡት ማጥባት ጊዜ ወደ ልጅሽ ያልፋሉ፡፡ እነዚህ ወታደሮች አንቲቦዲስ ይባላሉ፡ በአጭሩ በደም ውስጥ የሚገኙ በሽታ አምጪ ተህዋስያንን የሚዋጉልን ፕሮቲኖች ናቸው፡፡ የፎርሙላ ወተት የሚጠቀሙ ሕጻናት የጡት ወተት ከሚወስዱት ይልቅ በተደጋጋሚ ይታመማሉ ማለት ነው፡፡

የጡት ወተት ከዚህም ሌላ ብዙ ጥቅሞች አሉት፤ ከነዚህም ውስጥ የልጅሽን አንጀት የማነቃቃት ብቃቱ ይጠቀሳል፡፡ የጡት ወተት የሕጻኗን ሰገራ ስለሚያለሰልስላት በቀላሉ እንድትጸዳዳ ይረዳታል፡፡ ሕጻናት የፎርሙላ ወተትን ለማብላላት ከጡት ወተቱ ይልቅ ሁለት እጥፍ ጊዜ ይፈጅባቸዋል፤ ስለዚህ ፎርሙላን ሲወስዱ የሚመገቡበት ድግግሞሽም ይቀንሳል፤ ሰገራቸውም የጠጠረና ሽታ ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ 

ጡት ማጥባት የልጅሽን ጤና ከመጠበቅ ባለፈ ንቁ እና ብልህ እንድትሆንም ያስችላታል፡፡ ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ጡት የሚጠቡ ሕጻናት በፎርሙላ ወተት እና በሌላ መንገድ ምግባቸውን ካገኙት ሕጻናት የበለጠ የሰላ ጭንቅላት ይኖራቸዋል፡፡ የዚህም ምክንያቱ ጡት ማጥባት ለሕጻናት የአዕምሮ እድገት የሚያስፈልገውን ንጥረነገር በመያዙ ነው፡፡

ጡት ማጥባትን የፎርሙላ ወተት ከመጠቀም የተሻለ የሚያደርገው ሌላው ነገር ሁሌም ዝግጁ፣ ተስማሚ እና በምቹ የሙቀት መጠን የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ጡጦ ማጠብ፣ መቀቀል፣ መበጥበጥ፣ ወተቱን ማሞቅ ወዘተ የሚባል ነገር ባለመኖሩ ሰዓትሽንም ገንዘብሽንም ይቆጥብልሻል፡፡

ጡት ማጥባት ላንቺም ብዙ ጥቅም አለው፤ ከወሊድ በኋላ ሕጻኗ ያንቺን ጡት ስትጠባ ከማህጸንሽ የሚፈሰው ደም እንዲቀንስ ያደርግልሻል፡፡ ማህጸንሽም በፍጥነት ከእርግዝና በፊት ወደ ነበረው መጠን እንዲመለስ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ጡት የምታጠቢ ከሆነ ለጡት እና ሌሎች አንዳንድ ካንሰሮች ያለሽ ተጋላጭነት ይቀንሳል፡፡ ጡት ማጥባት ተፈጥሯዊ የእርግዝና መከላከያሽም እንደሆነ መዘንጋት የለብሽም፡፡

 

ጡት በማጥባት ወቅት ልጄን እንዴት ልያዛት?

የተሳሳተ የሕጻን አያያዝና አስተቃቀፍ ጡት ማጥባትን እንዳይሳካ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ የተሳሳተ አያያዝ እና የጡት አጎራረስ የእናቲቱን የጡት ጫፍ እና ጡቱን ራሱንም ሊጎዳ ይችላል፡፡

ለሁሉም እናቶች የሚመች አንድ ዓይነት አቀማመጥ እና የአያያዝ ስልት ማግኘት ከባድ ነው፤ ምክንያቱም ያንቺ የክንድ ርዝመት፣ እንዲሁም የጡትሽ ግዝፈት  ከሌሎች እናቶች ጋር ስለሚለያይ ነው፡፡ ለጓደኛሽ ወይም ለጎረቤትሽ በጥሩ ሁኔታ የሰራው ላንቺ ላይሰራ ይችላልና ላንቺና ለልጅሽ የሚመቸውን አያያዝና አቀማመጥ በሙከራ ድረሺበት፡፡

የትኛውንም ዓይነት አያያዝና አቀማመጥ ብትመርጪም ዋናው ነገር ክንድሽ እና ትከሻሽ ዘና ማለቱ እና ምቾት ማግኘትሽ፣ እንዲሁም  ሕጻኗን ወደ ራስሽ አስጠግተሸ እና ሙሉ በሙሉ ወደ ጡትሽ አዙረሽ መያዝ እንድትችዪ ማድረጉ ነው፡፡ በምታጠቢበት ጊዜ፣

  • የሕጻኗ አንገት ሙሉ በሙሉ ክንድሽ ላይ ይሁን (እስከ ትከሻዋ ድረስ) እጅሽ እስከ ሕጻኗ መቀመጫ መድረስ አለበት፡፡
  • የሕጻኗ ሰውነት ወዳንቺ ሰውነት ይጠጋ
  • የሕጻኗ አፍ በደንብ ይከፈት፤ ጡቱን ስታጎርሻት በመጀመሪያ ሕጻኗ አፏን በደንብ እንድትከፍት አድርገሻት በሙሉ አፏ እስከምትይዘው ድረስ በደንብ ማስገባት አለብሽ፡፡
  • አገጯ ጡትሽን መንካት አለበት፡፡

 

ልጄ በደንብ እየጠባች እንደሆነ እንዴት አውቃለሁ?

በአግባቡ እየጠባች ያለች ሕጻን ስትውጥ ትሰሚያታለሽ፤ ስትጠባም ጉንጯ ሞላ ያለ እንጂ ወደ ውስጥ የተጣበቀ አይሆንም፡፡ ስትጠባ ረጋ እና ዘና ትላለች፤ ስትጨርስም ራሷ ጡትሽን ትለቀዋለች፡፡ በዚህ ጊዜ አፏ እንደራሰ ማየት ትችያለሽ፡፡ የጡትሽ ጫፍም ስለአጠባብሽ ይናገራል፡ ልክ ልጅሽ ጠብታ ስትነሳ የጡትሽ ጫፍ መጠፍጠፍ ወይም የተቆነጠጠ አይነት መምሰል የለበትም፤ ሕጻኗ በትክክል ጎርሳ ከነበረ የጡትሽን ጫፍ ሳይሆን በደንብ ገባ አድርጋ ጡቱን ስለምትጎርስ የጫፉ ቅርጽ ያን ያህል አይለወጥም፡፡ ካጠባሽ በኋላ ጡትሽም ወተቱ ስለሚወጣ ለስለስ ይላል፡፡

ሕጻኗ ልጅሽን ስታጠቢ ታዲያ አንዱን ጡት ጨርሳ ሳትጠባ ወደሌላኛው ማዞር የለብሽም፡፡ወደ ሌላኛው ጡትሽ ከማዞርሽ በፊት አንዱ ጡትሽ ላይ እስከምትጨርስ ድረስ ፣ቢያንስ ከ5 እስከ 10 ደቂቃ አጥቢያት፡፡ (ገና አዲስ የተወለዱ ሕጻናት በአንድ ጡት ላይ እስከ 20 ደቂቃ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ፤ እያደጉ እና እየተለማመዱ ሲሄዱ ነው ከ5-10 ደቂቃ በአንድ ጡት ላይ የሚወስዱት፡፡) ይህን ስታደርጊ ሕጻኗ ልጅሽ በደንብ ንጥረነገር ያለውን ቆየት ብሎ የሚወጣውን ወተት እንድታገኝ ታደርጊያታለሽ፡፡

ሕጻናት አንድ ጊዜ ሲጠቡ ሁለት ዓይነት ወተትን ያገኛሉ፤ ልጅሽ ገና መጥባት እንደጀመረች የሚወጣው ወተት የስብ መጠኑ አነስተኛ የሆነ፣ የውሃ መጠኑ ደግሞ በዛ ያለ ስለሆነ የሕጻኗን ጥም ይቆርጥላታል፡፡ ትንሽ ቆይቶ የሚወጣው ወተት ግን የካሎሪ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ፣ ረሃቧን ሊቆርጥ የሚችል አይነት ነው፤ ስለዚህም ነው ‘የተመጣጠነ ወተት’ እንድታገኝ ልጅሽን አንዱ ጡት ላይ እስከምትጨርስ ድረስ ሳታጠቢ ወደሌላኛው ማለፍ የሌለብሽ፡፡

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

]]>
የቅድመ ወሊድ ዘረመል ምርመራ ምንድን ነዉ? https://srhr.yetenaweg.com/%e1%8b%a8%e1%89%85%e1%8b%b5%e1%88%98-%e1%8b%88%e1%88%8a%e1%8b%b5-%e1%8b%98%e1%88%a8%e1%88%98%e1%88%8d-%e1%88%9d%e1%88%ad%e1%88%98%e1%88%ab-%e1%88%9d%e1%8a%95%e1%8b%b5%e1%8a%95-%e1%8a%90%e1%8b%89-wha/ Thu, 09 Feb 2023 02:34:42 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3350 የቅድመ ወሊድ ዘረመል ምርመራ ምንድን ነዉ? (What is prenatal genetic testing?)

ጆኬቤድ ክንፈሚካኤል ሱጋ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ)

Jochebed kinfemichael Suga, 4th year medical student at myungsung medical college
Approved by: Dr. Misikir Anberbir (Gynecologist/Obstetrician)

ያንዳንዱ የሰዉነታችን አካል እንዴት እንደሚሰራ ለእያንዳንዱ ህዋሳቶቻችን መመሪያን የያዘ አካል ጂን እንለዋለን፡፡ በሰዉነታችን ዉስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ጂኖች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ጂኖች በክሮሞሶም ዉስጥ ተቀምጠዉ ይገኛሉ፡፡

የእነዚህ ክሮሞሶም መዛባት ወይም መጉደል በሌላ ጎን ደግሞ የአንድ ወይም የብዙ ጂኖች አቀማመጥ መዛባት የዘረመል ችግር (genetic disease) ያስከትላል፡፡

የቅድመ- ወሊድ ዘረመል ምርመራ ህፃኑ/ኗ ከመወለዱ/ዷ አስቀድሞ ሊኖር የሚችልን የዘረመል ችግርን ለማሳወቅ ይረዳል፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ በሀገራችን እንደዚህ አይነት ምርመራ የሚታዘዘዉ በእርግዝና ክትትል ወቅት ያልተለመዱ ግኝቶችን ሀኪሞች ሲያስተዉሉ ከዘረመል ጋር ግንኙነት ሊኖረዉ ይችላል ብለዉ ሲያምኑ ነው፡፡

የቅድመ-ወሊድ የመለያ ምርመራዎች ምንድን ናቸዉ (What are the types of prenatal screening tests?)

 

የቅድመ-ወሊድ የመለያ (screening) ምርመራዎች በእርግጠኝነት ያለዉን የዘረመል ችግር አለ ወይንም የለም ብለው መንገር አይችሉም። ሆኖም ግን የዘረመል ችግር የመኖር እድሉ ከፍተኛ ወይንም ዝቅተኛ እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ ሀኪሞች ያደረጓቸዉ እነዚህ የመለያ(screening) ምርመራዎች ከፍተኛ እድል መኖሩን የሚያሳዩ ከሆነ ችግሩን ወደሚያረጋግጡልን ጠለቅ ያሉ ምርመራዎች እንቀጥላለን፡፡

 

የክሮሞሶም መጠን መለያ ምርመራ (Screening for an abnormal chromosomal number)

እያንዳንዱ በሰዉነታችን ዉስጥ የሚገኙ ክሮሞሶሞች ጥንድ ጥንድ ሆነዉ ይገኛሉ፡፡ አንደኛዉ ጥንድ ከአባት አንደኛዉን ጥንድ ደግሞ ከእናት እናገኛለን፡፡ ፅንስ በሚፈጠርባቸው በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ዉስጥ እነዚህ ክሮሞሶሞች ጥንድ ሆነዉ አለመገኘት ወይም ከጥንዶቹ ተጨማሪ ክሮሞሶሞች መገኘት በፅንሱ ላይ ለሚታዩ ያልተለመዱ የምርመራ ግኝቶች ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለእነዚህም የምናደርጋቸዉ ምርመራዎች 

  •  Cell free fetal DNA screening—– ይህም ከእናት በሚወሰድ ደም ዉስጥ በመጠኑ የሚገኘዉን የፅንስ ዲኤንኤ በመመርመር፣ በልጁ ላይ ያልተለመደ ግኝት ሊኖር ይችላል ወይም አይችልም የሚለዉን ያሳየናል፡፡
  • Serum screening (የደም ምርመራ)……….. ከላይ እንደጠቀስነዉ አይነት ከእናትየው በሚወሰድ የደም ናሙና የሚሰራ ሲሆን ፤ ከመጀመሪያዉ የሚለየዉ ነገር በፅንሱ ምክንያት ተለቀዉ የሚገኙትን የተለያዩ ፕሮቲኖች መጠን በመለየት ፅንሱ ላይ ያልተለመደ ግኝት ሊኖር ይችላል ወይም አይችልም የሚለዉን ያሳየናል፡፡

 

የአካል ለዉጥ መለያ ምርመራዎች (Screening for physical abnormalities)

አንዳንድ ጊዜ በክሮሞሶሞች ላይ ያሉ ችግሮች የልጁ አካል ላይ የሚያሳዩት ለዉጥ ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህም በቅድመ-ወሊድ ክትትል ጊዜ በልጁ ላይ የሚስተዋል የአካል ለዉጥ ከክሮሞሶም ችግሮች ጋር የተያያዘ መሆን እና አለመሆኑን ለማረጋገጥ ምርመራዎች ይደረጋሉ፡፡

  1. የፅንሱ ከአንገት ጀርባ መፍዘዝ (nuchal translucency): በultrasound በሚደረግ የቅድመወሊድ ክትትል ጊዜ መጠነኛ የሆነ ቦታን የያዘ የአንገት ጀርባ መፍዘዝ፣ ከክሮሞሶም ጋር የተገናኘ የአካል ለዉጥ ሊኖር እንደሚችል ያሳያል፡፡
  2. ኤኤፍፒ ምርመራ (AFP screening)፡ ከእናትዬዉ በሚወሰድ የደም ናሙና ዉስጥ የኤኤፍፒ መጠን በመለካት የሚካሄድ ሲሆን መጠኑ ከተጠበቀዉ በላይ በልጦ ሲገኝ የፅንሱ የአካል ለዉጥ በሆድ ፣ በፊት ወይም በህብለሰረሰር ላይ የመሆን እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ይነግረናል፡፡
  3. ኳድ ስክሪን (QUAD screen)፡ ይህ ምርመራ ከእናትየው በሚወሰድ ደም የሚደረግ ሲሆን አራት አይነት ምርመራዎችን አካቶ ይይዛል፡፡
  4. (Fetal anatomy scan): ultrasound በመጠቀም የእያንዳንዱን የልጁን አካል ክፍሎች በመለካት ይካሄዳል፡፡ ብዙን ጊዜ ፅንሱ 18 ሳምንት እና ከዛ በላይ ከሆነ በኋላ የሚደረግ ምርመራ ነዉ፡፡

 

ምን አይነት አረጋጋጭ ምርመራዎች አሉ? (What type of prenatal diagnostic tests are there?)

 

ከላይ በጠቀስናቸዉ ምርመራዎች ያልተለመዱ ዉጤቶችን ወይም ደግሞ አጠራጣሪ ውጤቶችን እና ግኝቶችን በልጁ ላይ ሲስተዋል የክሮሞሶም ችግር አለ ወይም የለም የሚለዉን ነገር አረጋግጠዉ ወደሚነግሩን ምርመራዎች ይመሩናል፡፡

 

እነዚህም ምርመራዎች ፅንሱን አንሳፎ ከያዘዉ እንሽርት ውሀ ወይም ከእንግዴ ልጅ በሚወሰዱ ናሙናዎች የሚካሄዱ ናቸዉ፡፡

  • አምኒዎሴንቴሲስ (amniocentesis)፡ ከእንሽርት ዉሀ ከሚወሰድ ናሙና የፅንሱን ክሮሞሶም ችግር የትኛዉ ክሮሞሶም ላይ እንደሆነ፣ የክሮሞሶም ተባዝቶ መገኘት ወይስ ጥንድ ሆኖ አለመገኘት ወይም የጂኖች ትክክለኛ ቅደም ተከተላቸዉን አለመጠበቅ እነደሆነ ያለዉን ችግር በግልፅ የሚነግረን የምርመራ አይነት ነዉ፡፡ ይኽም የምርመራ አይነት በሙያዉ በሰለጠኑ ሀኪሞች የሚካሄድ ሲሆን በultrasound በመታገዝ ከማህፀኑ በመርፌ ከእንሽርት ውሀው ናሙና ተወስዶ ወደ ዘረመል ላብራቶሪ የሚላክ የምርመራ አይነት ነዉ፡፡ ይህ የምርመራ አይነት ፅንሱ ከ16-20 ሳምንት ባለበት ጊዜ ዉስጥ የሚካሄድ ነዉ፡፡
  • ሲቪኤስ (chorionic villus sampling, CVS): ከእንግዴ ልጅ በሚወሰድ ናሙና የፅንሱን የክሮሞሶም ችግሮችን በግልፅ ለማወቅ የሚደረግ የምርመራ አይነት ነዉ፡፡ይህ የምርመራ አይነት ፅንሱ ከ11-13 ሳምንት ባለበት ጊዜ ዉስጥ የሚካሄድ ሲሆን ከአምኒዮሴንቴሲስ በመጠኑ የበለጠ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል እና የናሙናዉ ጥራት ላይ ተፅዕኖ ሊኖረዉ ስለሚችል አብዛኛዉን ጊዜ በሀኪሞች ዘንድ አይዘወተርም፡፡
  • እነዚህ የምርመራ አይነቶች የዘረመል ላብራቶሪዎችን አስተዋፅኦ ስለሚጠይቁ ውጤቶቻቸዉ እስኪደርሱ ከ1-2 ሳምንታቶች ሊወስዱ ይችላሉ፡፡

የዘረመል ምርመራዎችን የሚያስፈልጋቸዉ እነማን ናቸዉ? (Who should get genetic testing?)

ለመለያ የሚደረጉ ምርመራዎችን ማንም እርጉዝ በፍላጎቷ ለማድረግ ወይንም ላለማድረግ መጠየቅ ትችላለች፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ምርመራዎች እንዲደረጉ አብዛኛውን ጊዜ በሀኪሞች በኩል የሚመከሩባቸዉ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸዉ፡፡

  •  እድሜያቸዉ ከፍ ካለ በኋላ የፀነሱ እናቶች ላይ አብዛኛዉን ጊዜ የክሮሞሶም ችግሮች ተያይዘዉ የመምጣታቸዉ እድል ከፍተኛ ስለሆነ ማንኛዉም እድሜዋ ከ35 በላይ የሆነች እርጉዝ ሴት የመለያ ምርመራዎችን ብታደርግ ይመከራል፡፡
  • ከዚህ በፊት ባሉ እርግዝናዎች ተከታታይ ዉርጃ ያጋጠማት ሴት 
  • ከዚህ በፊት ባሉ እርግዝናዎች የክሮሞሶም ችግር ያለበት ልጅ የተወለደ ከነበረ
  • በቅድመ-ወሊድ ክትትል ጊዜ የተስተዋሉ ከክሮሞሶም ችግር ጋር ሊያያዙ የሚችሉ ያልተለመዱ ግኝቶች  
  • ለመለያ የሚደረጉ ምርመራዎች በእናትየዋ ላይ ሆነ በፅንሱ ላይ የሚያስከትለዉ ምንም አይነት ጉዳት አይኖርም፡፡ ሆኖም ግን ለማረጋገጥ የሚደረጉ የአምኒዮሴንቴሲስ እና የሲቪኤስ ምርመራዎች የተወሰነ ተፅዕኖ ይኖራቸዋል፡፡ ቢሆንም ግን የሚያስከትሉት ተፅዕኖ በፐርሰንት ከ1% ያነሰ ስለሆነ ጉዳቶቻቸዉ ብዙም ጎልተዉ አይታዩም፡፡

 

#የቅድመ-ወሊድምርመራዎች  #የቅድመ-ወሊድዘረመልምርመራ #የክሮሞሶምችግሮች #የፅንስዘረመልምርመራዎች #አምኒዮሴንቴሲስ

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

]]>
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ (Gestational DM) https://srhr.yetenaweg.com/%e1%89%a0%e1%8a%a5%e1%88%ad%e1%8c%8d%e1%8b%9d%e1%8a%93-%e1%8c%8a%e1%8b%9c-%e1%8b%a8%e1%88%9a%e1%8a%a8%e1%88%b0%e1%89%b5-%e1%8b%a8%e1%88%b5%e1%8a%b3%e1%88%ad-%e1%89%a0%e1%88%bd%e1%89%b3-gestational-dm/ Thu, 09 Feb 2023 02:22:15 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3347 በ ሔቨን ምክሩ በሪሁን  (የ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የ 5ተኛ ዓመት የ ሕክምና ተማሪ )

Heaven Mekeru Berihun, ( 5 Year Medical Student at St.Paul Hospital Millennium Medical College )

Reviewed and Approved by Dr.Misikr Anberbir (Gynecologist/Obstetrician )

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ምንድነው?

 

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ የሚባለው አንዲት ከዚህ በፊት የስኳር በሽታ የሌለባት ነፍሰጡር ለመጀመሪያ ጊዜ በእርግዝና ወቅት የስኳር በሽታ እንዳለባት ሲረጋገጥ ነው። ልክ እንደሌሎች የስኳር በሽታ ዓይነቶች፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታም ህዋሶች(ሴሎች) ስኳር የሚጠቀሙበትን መንገድ ያስተጓጉላል።

 

 መንስኤው ምንድን ነው?

 

Placenta (የእንግዴ ልጅ) በማደግ ላይ ላለው ህጻን አልሚ ምግቦች እና ውሃ ይሰጣል በተጨማሪም እርግዝናን ለመጠበቅ የተለያዩ ሆርሞኖችን ያመነጫል።  እነዚህ ሆርሞኖች የሰውነቷ ሕዋሳት ኢንሱሊንን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ያደርጓቸዋል፣ እንደወትሮው ለኢንሱሊን መልስ መስጠትም ያቆማሉ። ይህም በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን እና የሰውነቷን የኢንሱሊን ፍላጎት ይጨምራል።

 

በእርግዝና ጊዜ ለሚከሰት የስኳር በሽታ አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

 

* ከእርግዝና በፊት ከመጠን ያለፈ ውፍረት መኖር

* አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ

*ከእርግዝና በፊት የቅድመ የስኳር (prediabetes) በሽታ መኖር

* በቀድሞ እርግዝና ወቅት በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ከነበረ

* የስኳር በሽታ ያለበት የቅርብ የቤተሰብ አባል መኖር

* ከዚህ ቀደም 4 ኪሎግራም (ከ9 ፓውንድ) በላይ የሚመዝን ህፃን ልጅ ከወለደች

 

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

 

ብዙ ጊዜ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም ግልፅ የሆኑ ምልክቶችን አያሳይም። ነገር ግን ቶሎ ቶሎ ውሀ የመጠማት እና ብዙ ጊዜ የሽንት መሽናት ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ።

 

እንዴት መከላከል ይቻላል?

 

በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር በሽታን ለመከላከል ከእርግዝና በፊትም ሆነ በእርግዝና ወቅት ጤናማ የአኗኗር ዘዴዎችን መከተል ጠቃሚ ነው።

 

* ጤናማ ምግቦችን መመገብ። በፋይበር የበለፀጉ እና ዝቅተኛ ስብ እና ካሎሪ ያላቸው ምግቦችን መምረጥ ጠቃሚ ነው። ፍራፍሬዎች፣አትክልቶች እና እህሎች ላይ በማተኮር የተመጣጠነ ምግብን መመገብ ይመከራል።

 

*  በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት እንደ የእግር ጉዞ ያሉ መጠነኛ እንቅስቃሴዎች ማድረግ

 

* ጤናማ በሆነ ክብደት እርግዝናን መጀመር፦ አንዲት ሴት ለማርገዝ እያሰበች ከሆነ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እና የአመጋገብ ልምድን በማስተካከል  ከመጠን ያለፈ ውፍረትን በመቀነስ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታን መከላከል ትችላለች።

 

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ምርመራ መቼ  ይሰራል?

 

የነፍሰጡሯን እና የልጇን ጤና ለመጠበቅና ህክምና ለመጀመር  በእርግዝና ጊዜ የስኳር በሽታ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

 

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ አብዛኛውን ጊዜ  የሚያጋጥመው በ24ኛው የእርግዝና ሳምንት አካባቢ ነው። ስለዚህ አንዲት ነፍሰጡር ለቅድመ ወሊድ ክትትል ወደ ጤና ተቋም ስትሄድ ተጋላጭነቷ ታይቶ በ24 እና 28 የእርግዝናዋ ሳምንታት መካከል ልትመረመር ትችላለች። ለዚህ ምርመራ ልዩ የተዘጋጀ ግሉኮስ ይወሰዳል። ከዚያም በመቀጠል በደምዋ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ይለካል።

 

ሕክምናው  ምንድነው?

 

በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ሕክምና በደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን መቆጣጠር እና በማህፀን ውስጥ የሚገኘውን ህፃን እድገትና ጤንነት መከታተል ላይ ያተኩራል። ጤናማ ምግብን በትክክለኛው ጊዜ መመገብ እና መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ይቀንሳል። እንዲሁም ሰውነታችን ኢንሱሊንን በአግባቡ እንዲጠቀም ያደርጋል። ጤናማ አመጋገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የደምን ስኳር  መጠን ለመቆጣጠር በቂ ካልሆኑ  መድሃኒት ሊጀመር ይችላል።

 

የሚያስከትላቸው ተዛማጅ የጤና ችግሮች ምንድን ናቸው?

 

* በእርግዝና ወቅት ለሚከሰት የደም ግፊት መጨመር ያጋልጣል።እንዲሁም በቀዶ ህክምና (C-section) የመውለድ እድልን ይጨምራል። 

 

ከዚህ በተጨማሪም የሚወለደውን ህፃን ለሚከተሉት ችግሮች ሊያጋልጥ ይችላል፦

 

* ከመጠን በላይ ውፍረት ያለው ህፃን ፦ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከመደበኛው መጠን ከፍ ያለ ከሆነ የልጁ ክብደት እንዲጨምር ያደርጋል። 4.1ኪሎ እና ከዛ በላይ የሚመዝኑ ህፃናት በወሊድ ጊዜ በማህፀን ውስጥ የመታፈን ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይህንንም ለመከላከል ሲባል በቀዶ ጥገና( C-section) የመውለድ እድልን ይጨምራል።

 

* ያለጊዜው መወለድ ፦ ቀደም ብለው የተወለዱ ሕፃናት የመተንፈሻ አካላት እድገታቸውን ስላልጨረሱ የመተንፈስ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል።

 

* ዝቅተኛ የደም ስኳር (hypoglycemia)፦ አንዳንድ ጊዜ ህፃናት ከተወለዱ ብዙም ሳይቆይ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ዝቅተኛ ይሆናል።በዚህ ጊዜ በፍጥነት የሕፃኑ/ኗን አመጋገብ በማስተካከል በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ወደ መደበኛው መመለስ አስፈላጊ ነው።

 

* የሚወለዱት ህጻናት ወደፊት ከመጠን ላለፈ ውፍረት እና ለዓይነት 2 የስኳር በሽታ ተጋላጭ ናቸው።

 

* ያልታከመ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት የስኳር በሽታ ልጁ ከመወለዱ በፊት በማህፀን ውስጥም  ሆነ ከተወለደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሕፃኑን ሞት ሊያስከትል ይችላል።

 

ብዙውን ጊዜ ልጁ ከተወለደ በኋላ በእናትየው ደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ወደ መደበኛው ይመለሳል። ሆኖም 50% የሚሆኑት የእርግዝና ወቅት የስኳር በሽታ የነበረባቸው ሴቶች ወደፊት በዓይነት 2 የስኳር በሽታ ይያዛሉ። የዚህን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከወሊድ በኋላ ጤናማ የሰውነት ክብደት እንዲኖራት ይመከራል። ከዚህ በተጨማሪም በየጊዜው ወደ ጤና ተቋም በመሄድ በደሟ ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መመርመር ተገቢ ነው።

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

]]>
ኤችአይቪ እና እርግዝና https://srhr.yetenaweg.com/%e1%8a%a4%e1%89%bd%e1%8a%a0%e1%8b%ad%e1%89%aa-%e1%8a%a5%e1%8a%93-%e1%8a%a5%e1%88%ad%e1%8c%8d%e1%8b%9d%e1%8a%93/ Tue, 29 Nov 2022 03:06:16 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3317 በ ጆኬቤድ ክንፈሚካኤል ሱጋ (ሚዩንግሱንግ ህክምና ኮሌጅ የ፬ አመት ተማሪ) / Jochebed Kinfemichael Suga, 4th year medical student at Myungsung Medical College

Approved by: Dr. Misikir Anberbir (Gynecologist/Obstetrician)

 

አንዲት ሴት እርጉዝ ሆና የቅድመ-ወሊድ ክትትል ስትጀምር ከሚደረግላት የመጀመሪያ ምርመራዎች ዉስጥ አንዱ የኤችአይቪ ምርመራ ነዉ፡፡ ይህንን ምርመራ ማድረግ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ከእናት ወደ ልጅ መተላለፊያ መንገዶችን በመቀነስ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መዉለድ እንዲያስችላት ነዉ፡፡

 

የቫይረሱ ከእናት ወደ ፅንሱ የመተላለፍ አቅሙ በብዙ ሁኔታዎች ላይ ይወሰናል፡፡ አጠቃላይ የኤችአይቪ ቫይረስ ስርጭት 15-45% ነው:: ከዚሀ ዉስጥ አንዲት የኤችአይቪ ቫይረስ በደሟ ውስጥ ያለ እናት ያለ ምንም ክትትል እና መድሃኒት የቫይረሱ መተላለፍ አቅም በእርግዝና ወቅት 10-15% ገደማ፣ በምጥ እና ወሊድ ወቅት ከ35-40%፣ ለረጅም ጊዜ ጡት በማጥባት ደግሞ ከ35-40% ገደማ እንደሆነ ያሳያሉ፡፡ ስለዚህ  አስቀድሞ የእናቶችን የቫይረሱ በደማቸዉ ዉስጥ መኖር እና አለመኖር ማወቅ አስፈላጊ ነዉ፡፡

ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ አቅም ብዙ አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሊጨምሩት አሊያም ሊቀንሱት ይችላሉ፡፡ የመተላለፍ አቅምን ከሚጨምሩ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ዉስጥ

  • የቫይረሱ መጠን በእናትዬዉ ደም ዉስጥ ጨምሮ መገኘት 
  • የእናትዬዉ CD4 መጠን ቀንሶ መገኘት 
  • እናትዬዉ ለቫይረሱ የተሰጣትን መድሃኒቶች በአግባቡ አለመዉሰድ
  • የእናትዬው በቂ እና ተመጣጣኝ ምግቦች አለመመገብ
  • የእናትዬዉ በሌሎች ተጨማሪ የተራቀቁ ወይም የከፉ በሽታዎች መያዝ
  • የእናትዬዉ በእርግዝና ወይም በምጥ ጊዜ በሌሎች ቫይረሶች ወይም ጥገኛ በሽታዎች መያዝ
  • የእናትዬዉ በሌሎች አባላዘር በሽታዎች መያዝ 
  • ለረጅም ጊዜ (በአማካይ ከ4 ሰአት በላይ) የቆየ የእንሽርት ዉሃ መፍሰስ
  • በወሊድ ጊዜ በእናትዬዉ ላይ የመውለጃ አካል (genital tract) ጉዳት ከደረሰ
  • ልጁ ከተወለደ በኋላ ለልጁ የሚሰጡ ድህረ ወሊድ እንክብካቤዎች መጉደል
  • ከ1 በላይ (የመንትያ) እርግዝና
  • ልጁ ከተጠበቀበት ጊዜ አስቀድሞ ከመጣ
  • ልጁ ሲወለድ ሊኖረዉ ከሚገባ የክብደት መጠን ቀንሶ ሲገኝ
  • ልጁ ከተወለደ በኋላ 6 ወር ሳይሞላዉ ተጨማሪ ምግቦችን ማስጀመር
  • ልጁን ከ2 አመት በላይ ማጥባት

ኤችአይቪ ቫይረስን ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ እንዴት እንከላከል?

የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በቫይረሱ ተይዘዉ የሚወለዱ ህፃናት ቁጥርን ለመቀነስ 4 ዋነኛ መከላከያ ስትራቴጂዋችን በማስቀመጥ ይሰራል፡፡

  1. አስቀድሞ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ለመቀነስ የሚደረጉ መከላከያዎች ላይ መስራት፡፡ ይህንንም በመቀነስ በቫይረሱ ቀድሞዉንም የተያዙ እናቶች ቁጥርን በመቀነስ ከቫይረሱ ጋር የሚወለዱ ህፃናትን ለመቀነስ የሚሰራ መከላከያ መንገድ ነዉ፡፡ ይህንንም ከግብ ለማድረስ ሰዎች የ”መ” ህጎችን ልማዶች እንዲያዳብሩ እና ቫይረሱን አስቀድሞ በማወቅ መድሃኒት ስለሚያስፈልጋቸዉ እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡
  2. ቫይረሱ በደሟ ዉስጥ ባለባት ሴት ያልታሰበ እና ያልታቀደ እርግዝና እንዳይኖር የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶችን በስፋት ለህብረተሰቡ ማስተማር
  3.  ቫይረሱ በደሟ ዉስጥ ያለባት ሴት ካረገዘች አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችን እና ቫይረሱ ወደ ልጁ ሊያስተላልፉ ከሚችሉ አሉታዊ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤን በመስጠት የመተላለፍ አቅምን መቀነስ ነው፡፡
  4. ቫይረሱ  በደማቸዉ ያለባቸውን እናቶች፣ የትዳር አጋሮች እና ልጆች አስፈላጊ የሆኑ እንክብካቤዎችን ለመስጠት የሚያስችል ክትትልን ማድረግ ነዉ፡፡

 

በቫይረሱ የተያዙ እናቶች በቅድመ እርግዝና ጊዜ ምን ማድረግ አለባቸዉ?

በቫይረሱ የተያዙ እናቶች በእያንዳንዱ ጤና ጣቢያ እና አብዛኛዉ ሆስፒታሎች የሚሰጡ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዲያገኙ ጠንክሮ ይመከራል፡፡ ይህንንም በማድረግ በዚህ ሰአት ልጅ ያስፈልገኛል? ያልታሰበ እና ያልታቀደ እርግዝናን ዉጤታማ በሆኑ መከላከያዎች እንዴት ማስቀረት እችላለዉ? ልጅ እንዲኖረኝ ሳስብ መጀመሪያ ላደርጋቸዉ የሚያስፈልጉ ነገሮች ምንድን ናቸዉ? ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ እንዲኖረኝ ሊኖረኝ የሚገባዉ የጤና ደረጃ ምንድን ነዉ? እና የመሳሰሉትን ሀሳቦች አገልግሎት ከሚሰጡ አካሎች ጋር በግልፅ መማከር የሚያስችል ይሆናል፡፡

            በቫይረሱ የተያዙ እናቶች በቅድመ ወሊድ ጊዜ ምን ይጠበቃል?

  • ከየትኛዉም እናቶች በላይ በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ሊሰጣቸዉ የሚገቡ እንክብካቤዎች የተለየ ጥንቃቄ እና ልዩ ትኩረት ስለሚያስፈለገዉ ማንኛዉም በቫይረሱ የተያዘች እናት አስፈላጊዉን የቅድመ-ወሊድ ክትትል ያለማቋረጥ እንድትከታተል ይመከራል፡፡ 

 

  • ማንኛዉም በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ለቫይረሱ የሚሰጡ መድሃኒቶች ከመጀመራቸዉ በፊት ድጋሚ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም አላስፈላጊ መድሃኒቶችን ሳያረጋግጡ ከመስጠት ለመቆጠብ የሚደረግ ጥንቃቄ ነዉ፡፡

 

  • በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ለቫይረሱ የተሰጣቸዉን መድሃኒቶች ያለማቋረጥ በአግባቡ መዉሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ 

 

  • ማንኛዉም ደረጃቸው ዝቅ ያሉ (low risk) የኤድስ ምልክቶች የሚያሳዩ እናቶች የኤችአይቪ ኤድስ እና የቅድመ ወሊድ ክትትል በሚያደርጉበት የጤና ማእከል መቀጠል ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ደረጃቸው ከፍ ያሉ (high risk) የኤድስ ምልክቶችን የሚያሳዩ እናቶች የኤችአይቪ ኤድስ ክትትላቸውን ወደ ኤችአይቪ ኤድስ ክትትል አገልግሎት ክፍል በማዘዋወር አስፈላጊዉን ክትትል እና በቅርብ ምልከታ መታየት ያስፈልጋቸዋል፡፡

 

  • በደሟ ዉስጥ ያለዉን የቫይረስ መጠን በማወቅ እየተሰጧት ያሉት መድሃኒቶች ረድተዋታል ወይስ አልረዷትም የሚለዉን በቅርብ መከታተል ያስፈልጋል፡፡

 

  • በቅድመ ወሊድ ጊዜም ከእናት ወደ ልጁ የሚተላለፍበትን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ከእናትዬዉ ጋር በመወያየት ለማስቀረት የሚሰሩ ስራዎችም መሰራት አለባቸዉ፡፡ የልጁ እድገትንም በአልትራሳዉንድ በመከታተል ፅንሱ የእድገት ዉስንነት አለዉ ወይስ የለዉም የሚሉትን ነገሮች ማየት ያስፈልጋል፡፡

 

በምጥ ወቅት የሚደረጉ ጥንቃቄዎች

  • ምጥ በሚጀምርበት ግዜ በቶሎ ወደ ጤና ተቋም መሄድ
  • ተደጋጋሚ የማህፀን ምርመራ አለማድረግ
  • የፅንስን ውሀ ከማፍሰስ መቆጠብ

 

ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለ እናቶች ላይ በድህረወሊድ ጊዜ ምን ይጠበቃል?

ማንኛዉም በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ለቫይረሱ የጀመሩትን መድሃኒቶች ሳያቋርጡ ከወሊድ በኋላም መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ በድህረወሊድ ጊዜ የተወለዱት ህፃናት ጡት ማጥባት ወይስ የፎርሙላ ወተት (በተለምዶ የጣሳ ወተት) ይጠቀሙ ለሚለዉ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመማከር የትኛዉ  ተቀባይነት አለው፣ ተመጣጣኝ፣ ዘላቂ፣ አዋጭ እና አስተማማኝ ነዉ የሚለዉን በማመዛዘን የሚወሰን ይሆናል፡፡

 

 በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች

  • በቫይረሱ የተያዘች ሴት ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መዉለድ ትችላለች?

አዎ፣ ትችላለች፡፡ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍ የሚችልበት ትልቅ አቅም ቢኖረውም የቫይረሱን መኖር ቅድሚያ በማወቅ በሚደረጉ መከላከያ መንገዶች ልጁ በቫይረሱ የሚያዝበትን አቅም መቀነስ ይቻላል፡፡

  • በቫይረሱ የተያዘች ሴት ጡት ማጥባት ትችላለች?

አብዛኛዉ አገራት በቫይረሱ የተያዙ እናቶች ጡት እንዲያጠቡ አይመክሩም፡፡ ነገር ግን ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረዉ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመማከር የሚወሰን ነዉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2010 ወቅት ላይ እንደጠቀሰዉ በቫይረሱ የተያዙ እናቶች እስከ 6 ወር ድረስ በእናት ጡት ብቻ እንዲቆዩ ይመክራል፡፡ ለረጅም ጊዜ (ከ 2 አመት በላይ) ጡት ማጥባት አይመከርም፡፡ 

  • ቫይረሱ ፅንሱ ላይ የሚያመጣዉ ተፅዕኖ አለ?

ፅንሱ ያለጊዜዉ መወለድ፣ የፅንስ ዉርጃ ወይም በማህፀን ዉስጥ መሞት፣ ፅንሱ ከሚጠበቅበት ክብደት አንሶ መወለድ እና የፅንስ እድገት ቅንጭርነት ብዙ ጊዜ ከሚጠቀሱ ተፅዕኖዎች ዉስጥ ዋነኞቹ ናቸዉ፡፡

  • ፅንሱ በቫይረሱ ላይ የሚያመጣዉ ተፅዕኖ አለ?

እርግዝና በቫይረሱ ላይ የሚያመጣዉ ምንም አይነት ተፅዕኖ የለም፡፡ የቫይረሱን ስርጭት አያብሰዉም ወይንም አይቀንሰዉም፡፡

 

  • የትኛዉ የመዋለጃ ሂደት ይመረጣል፣ በምጥ ወይስ ኦፕራሲዮን?

ብዙ ፅሁፎች እንደሚያሳዩት የቫይረሱ መጠን ጥቂት ከሆነ እና እናትዬዉ መድሃኒቶቿን በአግባቡ እየተከታተለች ከነበረ በምጥ መዉለድ ጥሩ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ አንዳንድ ፅሁፎች በወሊድ ወቅት ሊኖር የሚችልን ንክኪ ለመቀነስ ኦፕራሲዮን የተሻለ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ በምጥ ወይስ ኦፕራሲዮን ለሚለዉ ጥያቄ የቫይረሱ መጠን ታይቶ የሚወሰን ይሆናል።

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

]]>
የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ https://srhr.yetenaweg.com/%e1%8b%a8%e1%89%85%e1%8b%b5%e1%88%98-%e1%8b%88%e1%88%8a%e1%8b%b5-%e1%8b%a8%e1%8b%b0%e1%88%9d-%e1%88%98%e1%8d%8d%e1%88%b0%e1%88%b5-antepartum-hemorrhage-bleeding/ Sun, 27 Nov 2022 02:34:27 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3311 የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ (Antepartum hemorrhage/bleeding)

በፌበን በየነ (ጎንደር ዩ/ህ/ጤ/ሳ/ኮ የህክምና ተማሪ- C2)

Approved by: Dr. Misikir Anberbir (Gynecologist/Obstetrician)

የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ ማለት አንዲት ሴት እርግዝናዋ 28 ሳምንት ከሞላው በኋላ ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚያጋጥም በማህፀን በኩል የሚከሠት የደም መፍሰስ ነው። 

ይህ ክስተት በእርግዝና ጊዜ ከሚታዩ አደገኛ ምልክቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን ከእርግዝና ጋር ተያይዞ ከሚመጣ ግፊት አና ኢንፌክሽን ጋር በመሆን ለእናቶች ሞት ምክንያት በመሆን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ስለዚህም ማንኛዋም እርጉዝ ሴት የደም መፍሰስ ሲያጋጥማት ከእንግዴ ልጁ ጋር በተያያዘ እና በሌሎች ምክንያቶች ሊሆን ስለሚችል በአፋጣኝ አካባቢዋ ወደሚገኝ የጤና ተቋም እንድትሄድ ይመከራል።

የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ በማህፀን በኩል ከሚያጋጥመው የደም መፍሰስ ጋር ተያይዞ በሆድ አካባቢ ህመም እና እንደምጥ ያለ ስሜት ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን የተያያዥ ምልክቶች አለመኖር አደገኝነቱን አይቀንሰውም።

 

 

የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል ነገር ግን በዋነኝነት በሶስት እንከፍላቸዋለን ።እነርሡም :-

  1. የእንግዴ ልጁ ከፅንሱ ሲቀድም ወይም የእንግዴ ልጁ የማህፀኑን በር ሸፍኖ ሲገኝ (placenta previa)
  2. የእንግዴ ልጁ ከማህፀን ግድግዳው ሲላቀቅ (placental abruption)
  3. ሌሎች (ኢንፌክሽን፣ ፖሊፕ ፣ የማህፀን በር ካንሰር ፣ ወዘተ… )

 

ለቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው? 

     *እድሜያቸው ከፍ ብሎ የሚያረግዙ ሴቶች (በተለይ 35 አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ)

     *ከእርግዝና በፊትም ሆነ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚመጣ የደም ግፊት ያለባቸው ሴቶች

     *በቅድመ ወሊድና ያለጊዜው የሚያጋጥም የእንሽርት ውሀ መፍሰስ ያጋጠማቸው ሴቶች (preterm premature rupture of membranes)

     *ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች

     *ከዘህ በፊት በነበሩ እርግዝናዎች ላይ የደም መፍሰስ ያጋጠማቸው ሴቶች

     *ከዚህ ቀደም በኦፕሬሽን የተገላገሉ ሴቶች

     *ሁለት(መንትያ) እና ከዚያ በላይ ፅንስ የተሸከሙ ሴቶች 

     *በእርግዝና ወቅት በሆድ አካባቢ የሚደርሱ አደጋዎች እና የመሳሰሉት…

 

የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ የሚያጋጥማቸው ሴቶች በተቀረው የእርግዝና ጊዜያቸው፣ በወሊድ ወቅት እና ከወሊድ በኋላ በእናትየውም ሆነ በልጁ ላይ ብዙ ችግሮች  ሊያመጣ ይችላል። በፅንሱ ላይ ከሚያመጣቸው ችግሮች መካከል በማህፀን ውስጥ የፅንስ መሞት (intrauterine fetal death) እና የፅንስ እድገት መገደብ ይካተታሉ።

በእናትየው ላይ ከሚከሰቱት ችግሮች መካከል ደግሞ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ:-

       *የድህረ ወሊድ የደም መፍሰስ (postpartum hemorrhage)

       *ከወሊድ በኋላ የእንግዴ ልጁ ክፍል በማህፀን ውስጥ መቅረት

       *ያለጊዜው የሚመጣ ምጥ እና  ወሊድ

       *በኦፕሬሽን የመውለድ እድልን መጨመር

       *ተገቢው ሕክምና ካልተገኘ ደግሞ ማህፀኑን በቀዶ ህክምና እስከማጣት እና እስከሞትም ሊያደርስ ይችላል።

 

ስለዚህም እናቶች በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ጣቢያም ሆነ ሆስፒታል በመሄድ መደበኛ የሆነ የቅድመ ወሊድ ክትትል በማድረግና በተጨማሪም የቅድመ ወሊድ የደም መፍሰስ ሲያጋጥማቸው በአፋጣኝ ህክምና በማግኘት በእነርሱም ሆነ በልጃቸው ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ችግሮች ቀድሞ መከላከል ይችላሉ።

 

References

  • Addisu Assefa MD, Yitbarek Fantahun MD, Eyasu Mesfin MD. (July 2020). Maternal and perinatal outcome of APH at three teaching hospitals in Addis Ababa, Ethiopia. Ethiopian Journal of reproductive health. Volume 12(2),8.
  • William’s obstetrics 24th edition

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

 

]]>
ከማህፀን ውጭ የሆነ እርግዝና https://srhr.yetenaweg.com/%e1%8a%a8%e1%88%9b%e1%88%85%e1%8d%80%e1%8a%95-%e1%8b%8d%e1%8c%ad-%e1%8b%a8%e1%88%86%e1%8a%90-%e1%8a%a5%e1%88%ad%e1%8c%8d%e1%8b%9d%e1%8a%93ectopic-pregnancy/ Sun, 20 Nov 2022 00:53:49 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3298 ከማህፀን ውጭ የሆነ እርግዝና(Ectopic Pregnancy)

በሔርሞን እስራኤል   (በሀያት ህክምና ኮሌጅ PC1 የህክምና ተማሪ)

Approved by: Dr. Misikir Anberbir (Gynecologist/Obstetrician)

 

 ጤናማ  እርግዝና ማለት የሴት   ልጅ እንቁላል ከወንድ ልጅ ዘር ጋር በሚዳቀልበት ጊዜ በሴት ልጅ ማህፀን ውስጥ የዳበረ እንቁላል ተፈጥሮአዊ እድገቱን የሚቀጥልበት ሂደት ሲሆን ከዚህ ውጭ የሚፈጠር እርግዝና ከማህፀን ውጭ እርግዝና ይባላል፡፡ 

 

ከማህፀን ውጭ የሆነ እርግዝና ስንል ምን ማለታችን ነው?

 

ከማህፀን ውጭ የሆነ እርግዝና ስንል ምን ማለታችን ነው? 

  

ከማህፀን ውጭ የሆነ እርግዝና ማለት ከወንድ ዘር ጋር የተዳቀለው እንቁላል (የዳበረ እንቁላል) በማህፀን ቱቦ (እንቁላልን ከኦቫሪስ ወደ ማህፀን የሚወስደው ቱቦ) ውስጥ በመጣበቅ እድገት የሚፈፅምበት ሂደት ነው።  በማህፀን ቱቦዎች ውስጥ እርግዝና ሲከሰት ፅንሱ እድገቱን መቀጠል የማይችል እና  በቱቦዎቹ ውስጥ በቆየ ቁጥር ደግሞ በእናትየው ጤና ላይ አደጋ የሚያስከስት ይሆናል፡፡ 

 

1000 ከሚሆኑ እርግዝናዎች ውስጥ ከ5-7 በሚሆኑ እናቶች ላይ ይህ ችግር የሚታይ ሲሆን ችግሩ ከዚህ ቀደም አጋጥሙዋቸው የነበሩ ወይም የማህፀን ኢንፌክሽን ችግር የነበረባቸው እናቶች፤ሴቶች ላይ የመፈጠር እድል አለው። 

 

 

ከማህፀን ውጭ እርግዝና እንዲፈጠር ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ምን ምንድን ናቸው? 

  የተለያዩ ችግሮች ለበሽታው አጋላጭ መንስኤ ቢሆኑም ከብዙዎቹ ዋነኞቹ ግን 

  • በቀዶ ህክምና ወቅት የሚደርስ የማህፀን ቱቦ ጉዳት
  • በማህፀን ቱቦዎች ላይ የሚከሰት ኢንፌክሽን
  • የሆርሞን መዛባት 
  • ከዚህ ቀደም የተከሰተ የማህፀን ውጭ እርግዝና 
  • ሲጋራ ማጨስ
  • የአባላዘር በሽታዎች ጥቂቶቹ ናቸው። 

  

ከማህፀን ውጭ የሚፈጠር እርግዝና ምልክቶች ምን ምንድን ምናቸው? 

  • ያልተለመደ ቁርጠት 
  • ደም ወይም ቡናማ ፈሳሽ በማህፀን መፍሰስ 
  • ጐን አካባቢ እንዲሁም ሆድ ላይ ያልተለመደ ህመም 
  • ማቅለሽለሽ፤ማስመለስ 

 

እነዚህ ምልክቶች የተለመደና ጤናማ እርግዝና ላይ የሚከሰቱ ቢሆኑም እነዚህ ምልክቶች የታየባቸው እናቶች ክትትል እንዲያረጉ ይመከራል። 

 

ከማህፀን ውጭ የሆነን እርግዝናን እንዴት መከላከል ይቻላል? 

 ይህን የእርግዝና አይነት ሙሉ በሙሉ መከላከል ባይቻልም ሊፈጠር የሚችልበትን እድል መቀነስ ይቻላል። ከእነርሡም ውስጥ በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ መከላከያን መጠቀም፣ በማህፀን ቱቦዎች ላይ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችን በጊዜው  መታከም እና ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ለማጨስ ማቆም መሞከር ዋነኞቹ ናቸው። 

 

ከማህፀን ውጭ የሆነ እርግዝና (ectopic pregnancy) የማህፀን ቱቦ መቀደድን ሊያስከትል ይችላል ይህም በሚሆንበት ጊዜ ዘላቂ ችግር ስለሚያስከትል በጊዜ ህክምና ማድረግ ተገቢ ነው።

 

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

 

]]>
ለጡት ካንሰር የራስን ጡት የመመርመር ሂደት https://srhr.yetenaweg.com/%e1%88%88%e1%8c%a1%e1%89%b5-%e1%8a%ab%e1%8a%95%e1%88%b0%e1%88%ad-%e1%8b%a8%e1%88%ab%e1%88%b5%e1%8a%95-%e1%8c%a1%e1%89%b5-%e1%8b%a8%e1%88%98%e1%88%98%e1%88%ad%e1%88%98%e1%88%ad-%e1%88%82%e1%8b%b0/ Sun, 20 Nov 2022 00:11:06 +0000 https://yetenaweg.com/?p=3286  ለልቱ መገርሳ (በአ.አ.ዩ ህ/ጤ/ሳ/ኮ የ5ኛ አመት የህክምና ተማሪ) 

By Laltu Megerssa, a 5th-year medical student at Addis Ababa University, College of Health Science.

Approved by: Dr. Mulugeta Kassahun (Consultant General and Oncologic Cancer) 

 

የራስን ጡት ለጡት ካንሰር መመርመር ማለት ማንኛውም የቆዳ ለውጥ፣ እብጠት ወይም ሌሎች እክሎች በራስ ጡት ላይ መፈተሽ ማለት ነው። የጡትዎ ገጽታ በወር አበባ ኡደት፣ ልጅ በመውለድ፣ ክብደት በመቀነስ ወይም በመጨመር በእድሜ መግፋት እና በአንዳንድ መድሃኒቶችን ምክንያት ሊቀያየር ይችላል። 

ይሄንን ምርመራ መቼ ይከናወን?

የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች የወር አበባ ደም መፍሰስ ከጀመረ በሳምንቱ ያለው ቀን በየወሩ የወር አበባ ማየት ያቆሙ ሴቶች ደግሞ በየትኛውም ቀን በየወሩ ማከናወን አለባቸው የጡት እራስን መመርመርን በመደበኛነት ማካሄድ የጡት ካንሰርን በጊዜ ለመለየት አንዱ ጠቃሚ መንገድ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል። ይህም በሽታው በሰውነት ዉስጥ ሳይሰራጭ የህክምና እርዳታ በማግኘት የመዳን እድልን ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ነገር ግን ይህ ሂደት በህክምና ተቋማት በህክምና ባለሞያዎች የሚደረግ ምርመራን ስለማይተካ በተለይ ከአርባ አመት በላይ ያሉ ሴቶች በየአመቱ የማሞግራፊ ምርመራ ማድረግ አለባቸው። ይህም በእጅ በመዳሰስ ለመለየት የማይቻል እብጠት ወይም ምልክቶች ያላሳየ በሽታን ቀድመን እንድንለይ ይረዳናል።

ሂደት

     1. ከመስተዋቱ ፊት ለፊት ቆመው እጆችዎን በወገብዎ ላይ ያድር

 

በሁለቱ ጡቶች መካከል ያለውን ልዩነት ያረጋግጡ አንድ ጡት የመተለቅ የጡት ጫፍ ከሌላው ከፍ ያለ ወይም የታጠፈ መሆን፣ የጡት ጫፍ መሰርጎድ በጡት ጫፍ አካባቢ ተደጋጋሚ ሽፍታ ካለ ያስተውሉ 

 

   2. በመቀጠል እጅዎን ከራስዎ ጀርባ  አድርገው የጡት ጫፍ መጎተት ያስተውሉ።

 

 

   3. የቀኝ ጡትዎን እየመረመሩ ከሆነ ቀኝ እጅዎትን ከጭንቅላትዎ ጀርባ ያድርጉት እና ጡትዎን በግራ እጅዎ ይፈትሹ። በሁሉም የጡት ክፍሎች ላይ ለሚገኝ ማንኛውም እብጠት እንዲሰማዎ ጣቶችዎን ይጠቀሙ። ወደ ንፍፊት እጢ መስፋፋትን ለማረጋገጥ በብብት ስር ውስጥ እብጠት እንደሌለ ያረጋግጡ።  ከላይ የተጠቀሰውን በግራ ጡት ላይም ይድገሙት።

 

አንዳንድ የጡት ካንሰር ምልክቶች፡

  •  በጡት ወይም በብብት ውስጥ አዲስ እብጠት
  • የጡቱ ማበጥ
  • የጡት ቆዳ መቆጣት ወይም መሰርጎድ
  • በጡት ጫፍ አካባቢ ወይም በጡት ላይ መቅላት ወይም የቆዳ መፈርፈር
  • የጡት ጫፍ ወደውስጥ መገልበጥ ወይም በጡት ጫፍ አካባቢ ህመም
  • ከጡት ወተት በስተቀር የሚመጣ የጡት ፈሳሽ ወይም ደም
  • በጡቱ ቅርጽ ወይም መጠን ላይ ያለ ማንኛውም ለውጥ
  • በማንኛውም የጡት ክፍል ላይ ህመም
  • የቆየ ከሆነ ተጭማሪ ከጡት ዉጭ ምልክቶች

 

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ካንሰር ካልሆኑ ሌሎች የጡት ሁኔታዎች ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ ይችላሉ። ሆኖም  ግን እነዚህ ምልክቶች ካሉዎት ወዲያውኑ ወደ ጤና ማእከል በመሄድ ምርመራ ያድርጉ።

የጤና ወግ 

ጠቃሚ እና የተረጋገጠ መረጃ ለጤናዎ ።

የጤና ወግን በነዚህ ሊንኮች መከታትል ይችላሉ ።

https://linktr.ee/Yetena_Weg

]]>